ራስን ለመከላከል የሚያስችሉ መሳሪያ ያደረጉ ሜክሲካዊ ጋዜጠኞች፣ ሜክሲኮ ከተማ በሚገኘው ባልቡየና አጠቃላይ ሆስፒታል ውስጥ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት፣ ሚያዚያ 8፣ 2012 ዓ.ም ያስተዳደር ሰራተኞች ያሰሙት የነበረውን ተቃውሞ ሲዘግቡ የሚያሳይ ምስል (ኤ.ፍ.ፒ/ፓድሮ)::

የሲ.ፒ.ጄ የጥንቃቄ ምክሮች ፤ ስለ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አዘጋገብ

ግንቦት 12፣ 2013 ዓ.ም የተሻሽለ 

የዓለም የጤና ድርጅት ኮቪድ-19(ኖቭል ኮሮናቫይረስ) ዓለማቀፍ ወረርሽኝ መሆኑን መጋቢት 2፣ 2012 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡ የዓለማቀፉ ሁኔታ እየተሻሻለ በመጣ ቁጥር፣ ሀገራት፣ የጉዞ እቀባቸውን እና ሲውስዱ የነበሯቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች እያላሉ ወይም እያለዘቡ መጥተዋል። ይህም የሆነው፣ የተለያዩ የዜና ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፣ አዳዲስና ለየት ያሉ የኮሮና ቫይረሶች መገኘታቸውን እና የኮቪድ-19 ክትባት መረሃ-ግብር መጠናክርን ተከትሎ ነው። 

ሕዝብ ስለቫይረሱ ሊኖረው የሚገባውን ግንዛቤ በማስጨበጥና መንግስታት ቫይረሱን ለመዋጋት የሚደረጉትን ጥረቶች በማሳወቅ ረገድ፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ጋዜጠኞች ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ነው። በሲ.ፒ. ጄ እንደተዘገበው፣ ጋዜጠኞች ይህንን የሚያደርጉት፣ በብዙ ሀገራት ያሉ መንግስታት፣ በነፃነት የመዘገብንና መረጃ የማግኘትን ሂደት በሚያሰናክሉበት ሁኔታ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የሚዲያው አካላት፣ ከፍተኛ ጫናና ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ከጋዜጠኞች ጋር በሲ.ፒ. ጄ የተደረጉ ቃለ መጠይቆች እንደሚሳዩት፣የመገናኛ ብዙኃን አባላት፣ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ፣ ቃለ መጠይቅ ሲያደርጉና ስራቸውን በሚሰሩበት ቦታ በከፍተኛ ደረጃ ለቫይረሱ ተጋላጭ እየሆኑ ነው:: በቅርቡ የወጣው የሲ.ፒ.ጄ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣  ጋዜጠኞች የሳንሱር ችግር ገጥሟቸዋል፤ ለእስር ተዳርገዋል፤ በኮቪድ 19 የተነሳ መተዳደሪያቸውን አጥተዋል።

እራሳችንን በየጊዜው ከሚወጡ ምክሮችና ክልከላዎች ለማስተዋወቅ/ለማዘመን፣ እኛ ሰለወረርሽኙ የምንዘግብ ጋዜጠኞች የዓለማቀፉ የጤና ደርጅት እና የየአካባቢያችን የጤና አካላት የሚያወጧቸውን መረጃዎች በአንክሮ ልንከታተል ይገባል። 

የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲ.ዲ.ሲ) እንዳስገነዘበው፣ ክትባት የወሰዱ የሚዲያ ሰራተኞችም ቫይረሱን ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ልብ ሊሉ ይገባል፤ የል ሜዲሲን እንደሚለውም፣ የተለያዩ ክትባቶች፣ የተለያዩ የቫይረሶችን ለመከካላከል ያላቸው አቅም ይለያያል። ስለሆነም፣ ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እና የአፍና-አፍንጫ መልበስ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎች እንደቀጠሉ ሊቆዩ ይገባል። 

በተጨማሪም፤ እኛ ሰለወረርሽኙ የምንዘግብ ጋዜጠኞች፣ የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ የመረጃ ማዕከል፣ ስለአሁናዊ የቫይረሱ ስርጭት ለማወቅ አስተማማኝ ምንጭ መሆኑን ማወቅ ጠቃሚ ነው።

በመስክ ስራ ላይ እራስን ከአደጋ ጠብቆ ስለመቆየት

የዓለማቀፍ የጉዞ እገዳዎች እና የጥንቃቄ-ነክ እርምጃዎች በየጊዜው ይቀያየራሉ፡፡ ያለበቂ ወይም ያለምንም ማሳሰቢያ፣ የዘገባ ስራዎች ሊለወጡ ወይም ሙሉ በሙሉ ሊሰረዙ ይችላሉ፡፡

ስለዚህ፣የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዘገብ የሚሹ ባለሙያዎች የሚከተሉትን የጥንቃቄ መረጃዎች ልብ ሊሉ ይገባል፤

ከስራ ሥምሪት በፊት

  • ማግኘት የምንችል ከሆነ፣ በተለይ የቫይርሱ ስርጭት ከፍተኛ ወደ ሆነባቸው ቦታዎች ለስራ መሄድ ወይም መጓዝ ካለብንና መከተቡ ችግር አያመጣብንም ብለን ካሰብን፣ አስቅድመን ክትባቱን መውሰድ ይኖርብናል።
  • የቫይረሱን የስርጭት አደጋ ወይም ተጋላጭነት ለመቀነስ፣ የምንገኝበትን ቦታ ወይንም መዳረሻችን ዘንድ ያለውን የቫይረሱን የስርጭት መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቃለ መጠይቆችን በአካል ከማድረግ ይልቅ በኢንተርኔት ወይንም በስልክ ማካሄድ ይኖርብናል፡፡
  • የአሜሪካው በሽታን የመቆጣጠሪያና የመከላከያ ማዕከል (ሲ.ዲ.ሲ) እንደሚለው፣ በዕደሜ የገፉ ሰዎችና እንደ ሰኳር በሽታ ያለ የቆየ የጤና እክል ያለባቸው ግለስቦች ወይም ያለቅጥ የወፈሩ ሰዎች ለቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጡ ወገኖች ናቸው፡፡ ከእንዲህ ዓይነት ሰዎች ጋር ቀጥተኛ ንክኪ የነበረን የመገናኛ ብዙኃን ሰራተኞች ከሆንን፣ የበሽታውን ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ከተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል ጋር በቀጥታ ሊያገናኘን የሚችል የዘገባ ሥራን ልናስወግድ ይገባልለነፍሰ ጡር ሰራተኞችም ተመሳሳይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡
  • በኒው ዎርክ ታይምስ እንደተገለጸው፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የሚዘግቡ ጋዜጠኞችን ሲመድቡ የዘረኝነት ጥቃት እንዳይካሄድባቸው ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ 
  • የዓለማቀፍ የጉዞ እቀባና ከቤት ያለመውጣት ድንጋጌዎች ያለበቂ ወይም ያለምንም ማስጥንቀቂያ ሊቀየሩ ይችላሉ።  በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ሥራ ላይ እያለን ልንታመም፣ እራሳችንን አግልለን ማቆይት ሊኖርብን፣ ወይንም ደግሞ ለረጅም ጊዜ ማግለያ ቦታ እንድንቆይ ልንገደድ ስለምንችል፣ እንደዚህ አይነት ችግር ቢገጥመን፣ ሊደረግልን ስለሚችለው እርዳታ መስሪያ ቤታችን ስላለው ዕቅድ፣ ከአለቆቻችን ጋር መወያየት ይኖርብናል። 

ስነልቦናዊ ደህንነት

  • በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የሮይተርስ ኢንስቲትዩት እንደገለጸው፣ ከፍተኛ ልምድ ያለቸው ጋዜጠኞች ሳይቀሩ፣ ስለ ኮቬድ-19 ሲዘግቡ፣ በስነልቦና ረገድ ሊቸገሩ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ፣ የስራ ሃላፊዎች፣ጋዘጠኞቻቸው እንዴት እየዘገቡ እነደሆነና እስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መመሪያና ድጋፍ ሊሰጧቸው ይገባል፡፡ 
  • በኮቪድ-19 ከተጠቃ ቦታ ወይም አካባቢ፣ በተለይም ከህክምና ተቋም ወይም ከቤት ያለመውጣት ድንጋጌ በተላለፈባቸው ቦታዎች ሆነን የዘገባ ስራ ስንሰራ፣ ሊፈጠር የሚችለውን የስነ-ልቦና ጫና ልብ እንበል። የዲ.ኤ.አር.ቲ ማዕከል ስለ ጋዜጠኝነት እና ጭንቀት (the DART Center for Journalism and Trauma) የተባለው የመረጃ ምንጭ፣ አስጨናቂ ሁኔታዎችን ለምንዘግብ ጋዜጠኞች ጠቃሚ ማዕከል ነወ። የአዕምሮ ጤናን ጨምሮ፣ ለጥንቃቄ የሚበጁ ምንጮችን ለማግኘት፣ የሲ.ፒ.ጄን የአደጋ ጊዜ ገጽ እንጎብኝ/እንምልከት

በቫይረሱ መለከፍን እና ቫይረሱን ወደ ሌሎች ማስተላለፍን መከላከል

በአሁኑ ጊዜ፣ በጣም ብዙ ሀገራት፣ ማሕበራዊ/ አካላዊ ርቀትን ተግባራዊ ማድረግ እንደቀጠሉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ፣ የሚመከረው የርቀት መጠን እንደምንግኝበት ሀገር ሊለያይ ይችላል። ባደጋ ጊዜ አገልግሎት ወደሚሰጥባቸው ወይም ከዚህ በታች ወደ ተገለጹ፣ የስጋቱ መጠን ከፍ ወዳለበቸው፣ ወደሚክተሉት ቦታዎች ሄደን ስለ ቫይረሱ ስንዘግብ፣ በቦታዎቹ ስለሚደረጉ የንጽህና አጠባበቆች በቅድሚያ በቂ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡ ስለሁኔታው የምንጠራጠር ከሆነ፣ ወደ እነዚህ ቦታዎች መሄድ የለብንም፤

ራሳችንን ከቫይረሱ ለመከላከል የሚያስችሉን መደበኛ ምክረ ሃሳቦች ደግሞ የሚከተሉትን ያካትታሉ፤

  • በየአካባቢው ባለስልጣናት በሚነገረን የርቀት መጠን መሰረት ከማንኛውም ሰው አካላዊ ርቀታችን እንጠብቅ። የመተንፈሻ አካላት ህመም ምልክቶች (ማስነጠስ ወይም ማሳል) የታዩባቸው ሰዎች ጋር ስንሆን፣ አዛውንቶችን፣ ከዚህ በፊት የቆየ በሽታ ያለባቸውን፣ በቫይረሱ ከተለከፉ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸውን፣ የቫይረሱ ምልክት ያለባችውን፣ የቫይረሱ ታማሚዎችን ሲያክሙ ከነበሩ የጤና ባለሙያዎችን ወይንም ለቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ የተጋለጡ ቦታዎች ውስጥ የሚሰሩ ሰዎችን ስናነጋግር ደግሞ የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። 
  • ቃለ መጠይቅ ሰናደርግ፣ ከቤት ውጭ ለማድረግ እንሞክር። ቃለ መጠይቁን እቤት ውስጥ ማድረግ ካለብን፣ አየር በደንብ የሚዘዋወርበት ስፍራ (ለምሳሌ መስኮቶቹ የተከፈቱበት) እንምረጥ፤ የተጣበበ ቦታን እናስወግድ።
  • ቃለ መጠይቅ በምናደርግበት ጊዜ፣ በተጠያቂዎቹ ፊት ለፊት ከመሆን ይልቅ፣ በሰያፍ በመቆም ቢያንስ ሁለት ሜትር እራሳችንን በማራቅ ስራችንን እንስራ፡፡ 
  • ከማንም ሰው ጋር እጅ መጨባበጥን፣ መተቃቀፍን እና መሳሳምን እናስወግድ። 
  • እጆቻችንን ለ20 ሴኮንዶች በሳሙናና በሞቀ ውኃ አዘውትረን በደንብ መታጠብና እጆቻችንን በሚገባ ማድረቃችንንም ማረጋገጥ፡፡ እጅን በደንብ ስለ መታጠብና ማድረቅ የሚያስረዳ መመሪያ በዓለም የጤና ድርጅት ድህረ-ገጽ ላይ ይገኛል፡፡
  • ሙቅ ውኃና ሳሙና በአካባቢው ከሌለ፣ ሳኒታይዘር ወይም ለዚሁ የተዘጋጁ መጥረጊያዎችን መጠቀም ይቻላል። ይሁንና፣ በተገኘው አጋጣሚ፣ወዲያውኑ በሞቀ ውኃና ሳሙና መታጠብ ግድ ይላል፡፡ (በዚህ ረገድ፣ከ60% በላይ ኢታኖል ወይም ከ70% አይዞፕሮፓይል የተዘጋጁ ሳኒታይዘሮች ውጤታማ እንደሆኑ ሲ.ዲ.ሲ ይመክራልሳኒታይዘርን መጠቀም በምንም አይነት አዘውትሮ እጅን መታጠብን ሊተካ እንደማይችል ላፍታ እንኳ መዘንጋት የለብንም፡፡
  • ስናስል ወይም ስናስነጥስ ሁሌም አፋችንን መሸፈን አስፈላጊ ነው፡፡ ስናስል ወይም ስናስነጥስ ሶፍት ከተጠቀምን፣ ሶፍቱን ወዲያውኑ በጥንቃቄና በተገቢ ሁኔታ ማስወገድ አለብን፡፡ ይህንን ካደረግን በኋላም እጃችንን በሚገባ መታጠብ ይኖርብናል፡፡
  • ፊትን፣ አፍንጫን፣ አይንና ጆሮን ወ.ዘ.ተ አለመንካት፡፡
  • ሌሎች ሰዎች በተጠቀሙበት መጠጫ ወይም የምግብ መመገቢያ እቃዎች አለመጠቀም፡፡
  • መላ ጸጉራችን መሸፈን አለበት። ጸጉራችን ረጅም ከሆነ ደግሞ በደንብ መታሰርና መጠቅለል ይኖርበታል።
  • የኮቪድ-19ን ስርጭት መዘገብ ከመጀመራችን በፊት ጌጣ ጌጦችንና የእጅ ሰዓቶችን አወላልቀን ማስቀመጥ፡፡ ይህን ማድረግም የሚያስፈልገን፣ ቫይረሱ በተለያዩ እቃዎች ላይ ለሰዓታት በሕይወት መቆየት ስለሚችል ነው።
  • መነጽር የምናደርግ ከሆነም፣ አዘውትረን በውኃና በሳሙና ማጽዳት፡፡
  • ከተቻለ፣ሥራ ላይ ስንሆን ዓይን ዉስጥ የሚሰኩ ሌንሶችን (contact lenses) ከማድረግ እንቆጠብ፤ ሳናስበው ዓይኖቻችንን ስንነካካ ሌንሶቹን መነካካታችን ስለማይቀር በቫይረሱ የመያዛችን ዕድል ከፍ ይላል፡፡ 
  • የምንለብሳቸውን የልብስ አይነቶች ስንመርጥ የትኞቹ የልብስ ዓይነቶች በቀላሉ ሊታጠቡ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡ ሥራችንን ከጨረስንም በኋላ፣ የተጠቀምንባቸውን ልብሶች በጥንቃቄ መነሳታቸውንና በሙቅ ውኃና በሳሙና በደንብ መታጠባቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡
  • ከተቻለ፣ ወደ ስራ ስንሰማራ ጥሬ ገንዘብ ከመያዝ እንቆጠብ፤ በተጨማሪም፣ ክሬዲት/ዴቢት ካርዶቻችንን፣ የብር መያዣ ወይንም ሌሎች ቦርሳዎቻችንን በየጊዜው በደንብ እናፅዳ፤ በተቻለ መጠን እጃችንን ኪሳችን ውስጥ አናስግባ/አንክተት፤
  • ወደተሰማራንበት ሥራ ለመሄድ ወይም ከዚያ ለመመለስ የምንጠቀምበትን የመጓጓዣ ዓይነት ከግምት ውስጥ ማስገባት አለብን፡፡ በተቻለ መጠን፣ የብዙኃን መጓጓዣዎች በሚጨናነቁበት ሰዓት መጓጓዝን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ ጉዟችንን እንደጨረስን፣ በሳኒታይዘር እጆቻችንን መጠራረግ ተገቢ ነው፡፡ 
  • በየሥራችን ጣልቃ እረፍት መውሰድ እንዳለብን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም፡፡ በሥራ የተዳከሙ ሰዎች ንጽህናቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ሊረሱ ይችላሉ፡፡ ለሥራ ወደ ተስማራንበት ቦታ ስንሄድ ወይም ስንመለስ ለረጅም ሰዓት ማሽከርከር ሲኖርብን ደግሞ፣ ሁኔታው ከዚህ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡

ራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ የህክምና መሳሪያዎች

የሚዲያ ሠራተኞች፣ የሚዘግቡትን ነገር በጥንቃቄ ለመዘገብ፣ የተሰማሩበትን የስራ ፀባይ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ እራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ማድረግ/መልበስ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ የህክምና መሳሪያዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ፤ ተጠቅመን የምንጥላቸው ጓንቶች፣ የፊት ጭንብሎች፣ የመከላከያ ሽርጦች፣ቱታዎች/በመላ አከላችን የሚጠለቁ ልብሶች እና ተጠቅመን የምንጥላቸው የጫማ መሸፈኛዎች።

እነዚህን ቁሳቁሶች በአግበቡ ለማጥለቅና ለማውለቅ ደግሞ መልካም የጥንቃቄ ተሞክሮዎችና የአጠቃቀም መመሪያዎችን በትክክል መከተልን ይጠይቃል፡፡ በሲ.ዲ.ሲ የተዘጋጀውን አጠቃላይ መመሪያ ለመመልከት ይህንን እንጫን፡፡ ብክለትን ከአንዱ ወደ ሌላው የማስተላለፍ አደጋ ከፍተኛ ስለሆነ፣ እነዚህን መመሪያዎች ከመተግበር ልንዘናጋ አይገባም፡፡ ከተጠራጠርን፣ ወደ ስራ ከመሰማራታችን በፊት የባለሙያ መመሪያ እና ስልጠና እንጠይቅ።

በብዙ ሀገሮች፣ አሁንም ጥራታቸውን የጠበቁ እራሰን ለመከላክል የሚያግለግሉ የህክምና መሳሪያዎች ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት ሊኖር ይችላል፤ መሳሪያዎቹን ማግኘትም አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም፣ እነዚህን መሳሪያዎች መጠቀማችን እጥረቱን ሊያባብስው እንድሚችል ልብ እንብል።

  • ራስን ለመከላክል የሚያግለግሉ የህክምና መሳሪያዎች ልካችን መሆናቸውን እናረጋግጥ። ልካችን ያልሆኑ መሳሪያዎች ሊቀዳደዱ ይችላሉ፤ በጣም ከጠበቡን፣ እንቅስቃሴያችንን ሊያውኩ፣ በጣም ከሰፉን ደግሞ፣ እንደ በር እጀታ ካሉ ነገሮች ጋር እየተያያዙ ሊቀዳደዱብን ይችላሉ።
  • ሁሌም እውቅና ባላቸው ድርጅቶች የተመረቱ እና የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ራሰን ለመከላከል የሚያገለግሉ የህክምና መሳሪያዎችን እንጠቀም፤ ይህንንም ስናደርግ፣ ለጥንቃቄ የተቀመጡ  መስፈርቶችን ማሟላት አለማሟላታቸውን እናረጋግጥ፡፡ የማይረቡና ተመሳሳለው  የተሰሩ ቁሳቁሶች ገባያውን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ልብ እንበል፡፡ ገበያውን አየመሩ ካሉና ከፍተኛ እውቅና ካገኙ እራስን ለመከላከል ከሚያገልግሉ ቁሳቁሶች መካከል ከፊሎቹን እዚህ ማየት ይቻላል፡፡
  • በቫይረሱ በተበከሉ እንደ ህከምና መስጫ ባሉ ተቋማት መስራት ወይም መሄድ ሲኖርብን፣ የመከላከያ ጓንቶችን ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከላቴክስ (latex) ጓንቶች ይልቅ፣ የኒትሪል (nitrile) ጓንቶች የተሻለ የመከላከል አቅም እንዳላቸው እንገንዘብ።
  • በጣም አስጊ በሆኑ እንደ ህከምና መስጫ ባሉ ተቋማት የዘገባ ሥራ መስራት ሲኖርብን፣ እራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ እንደ የፊት ጭንብሎችና በመላ አካል የሚጠለቁ ልብሶች ያሉ ተጨማሪ ቁሳቁሶችን መያዝ የግድ ይላል፡፡  
  • እንደየሥራ ጠባይችን፣ ተጠቅመን የምናስወግዳቸው ጫማዎች ወይም ከጫማ በላይ የሚጠለቁ ውኃ የማያበላሻቸው ነገሮች ማድረግ ሊኖርብን ይችላል፡፡ ቦታዎችን ስንለቅ፣ ሁሉንም በደንብ መጥረግ/ማለቅለቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ውኃ የማያበላሻቸውን ከጫማ በላይ የሚጠለቁ ነገሮችን ከተጠቀምን በኋላ፣ ቦታውን ከመልቀቃችን በፊት በጥንቃቄ ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡
  • ራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ስናደርግ/ስንለብስ፤ የሰለጠነ የባላሙያ ድጋፍ እንዲኖረን ይመከራል። ይህንን የምናደርገው፣ ከጥንቀቄ ጉድለት ሊከሰት የሚችለውን ለቫይረሱ የመጋለጥ አደጋ ለመቀነስ ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣ ይህን አለባበስ/አደራረግ እና አወላለቅን የሚያሳየውን ከሲ.ዲ.ስ. የተገኝውን ቪዲዮመመልከት ይበጃል፡፡ ይሁንና፣ ቪዲዮው ስልጠናን/የባለሙያ ድጋፍን ሊተካ እንደማይችል ልብ ይሏል፡፡
  • አንድ ጊዜ ብቻ እንድንገለገልባቸው የተሰሩ ራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ የህክምና መሳሪያዎች (ለምሳሌ ጓንቶች፣ በመላ አካል የሚጠለቁ ልብሶች ፣ ሽርጦችን ወይንም የጫማ መሸፈኛዎችን) በምንም አይነት መልስን መጠቀም የለብንም፡፡ መልስን ልንጠቅምበት ያሰብነውን መሳሪያ ከብክለትና ከጀርም ማጽዳት ይኖርብናል። በቫይረሱ የተጠቃውን ቦታ ከመልቀቃችን በፊትም፣እራስችንን ለመከላከል የተገለገልንባቸውን የተበከሉ የህክምና ቁሳቁሶች ባግባቡ ማስወገዳችንን እናረጋግጥ፡፡

የፊትና የአፍንጫ ጭንብሎች

የፊት ጭንብልን ባግባቡ መጠቀም፣ በተለይ ከማህብረሰቡ መካከል ሆነው ከተፋፈጉና በሰው ከተጨናነቁ ወይንም ለቫይረሱ በከፍተኛ ደርጃ ተጋላጭ ከሆኑ ስፍራዎች የሚገኙ የማህብረሰብ አባላትን እያነጋገሩ ለሚዘግቡ የሚዲያ ሰራተኞች በጣም አሰፍላጊ ነው። በተፋፈጉ ስፍራዎች፣ የቫይረሱ ጠብጣዎች መጠን ከሌሎች ቦታውች ከፍ ሊሉ ስለሚችሉ፣ በቫይረሱ የመያዝ እድላችን በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምርው እንደሚችል ልብ ልንል ይገባል። 

ባግባቡ ካልተጠቀምንባቸው ፣ የፊት ጭንብሎች በቫይረሱ ለመለከፍ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች እንዳሉ ልብ እንበል፡፡ ላንሴት (Lancet) ያደረገው አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በቫይረሱ በተጋለጠ አካባቢ የተደረገ የህክምና የፊት ጭንብል፣ ቫይረሱን ለሰባት ቀናት ይዞ ሊቆይ ይችላል፡፡ ይህ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ጭንብልን ማድረግ፣ መልሶ መጠቀም ወይንም  ጭንብሉን እንዳደረጉ ፊትን መነካካት ራስን ለቫይረሱ በከፈተኛ ደረጃ ማጋለጥ ማለት ሊሆን ይችላል።

የፊት ጭንብልን የግድ ማድረግ ካለብን ደግሞ፣ የሚከተሉትን ምከሮች መተግበር የግድ ይላል፤

  • ከተፋፈገ ቦታ፣ ከስዎች ጋር ተጠጋግተን ወይንም ለበሽታው በከፈተኛ ደርጃ ከተጋለጠ ስፍራ ሆነን የምንዘግብ ከሆነ፣ ከህክምና ጭንብል ይልቅ፣ ኤን 95ን (ኤፍ. ኤፍ.ፒ/ኤፍ.ኤፍ. ፒ3ን) መጠቀም ይመክራል።
  • የምናደርገው ጭንብል፣ የአፍንጫችንን የላይኛውን ጫፍና የአገጫችንን ጠርዝ መሸፈኑን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ይህም፣ የምናደርጋቸው ጭንብሎች ፊታችን ላይ በደንብ ልክክ እንዲሉ ያግዘናል
  • በተጨማሪም ጭንብሉ በደንብ መወጠሩንና በመሀል ክፍተት አለመኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
  •  የምናደርገው የፊት ጭንብል ፊታችን ላይ ልክክ እንዲልልን፣ ጺማችንን መላጨት ይኖርብናል፡፡ 
  • ካደረግነው በኋላ፣ ጭንብሉን መንካት የለብንም፡፡ ጭንብሉን ልናስወግድ ስንፈልግም ማሰሪያውን ብቻ በመጠቀም መሆን አለበት፡፡ ፊት ለፊት ያለውን የጭንብሉን አካል በጭራሽ መንካት የለብንም፡፡
  • የተጠቀምንበትን ጭንብል በጭራሽ በድጋሚ መጠቀም የለብንም፡፡ የተጠቀምንበት ጭንብልም ወዲያውኑ ክዳን ባለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ መጣል አለብን፡፡
  • የፊት ጭንብሉን ካስወገድን በኋላ፣ እጆቻችንን በሳሙናና በሙቅ ውኃ መታጠብ አለብን፡፡ ወይም ደግሞ፣ የአልኮል ሳኒታይዘር(60% በላይ ኢታኖል ወይም 70% አይዞፕሮፓይል)ተጠቅመን እጆቻችንን ልናፀዳ ይገባል፡፡
  • ጭንብሉ እርጥበት ሲያገኝው፣ በአዲስ፣ በንፁህና በደረቅ ጭንብል መተካት ተገቢ ነው፡፡
  • ጭንብልን መጠቀም፣ራሳችንን ከምንከላከልባቸው መንገዶች አንዱ ብቻ መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ ከጭንብሉ በተጓዳኝ፣ እጆቻችንን አዘውትረን በሙቅ ውኃና በሳሙና መታጠብና ፊታችንን፣ ማለትም ዓይኖቻችንን፣ ጆሮዎቻችን እና አፍንጫችንን ከመነካካት መቆጠብ አለብን፡፡
  • እንደ አካባቢው ሁኔታ፣ የፊት ጭንብል እጥረት ወይም የዋጋ ማሻቀብ ሊያጋጥም እንደሚችል ልንገነዘብ ይገባል፡፡

መሳሪያዎችን በጥንቃቄ ስለመያዝ

ኮቪድ 19 በቫይረሱ በተበከሉ መሳሪያዎች አማካኝነት የመዛመት እድሉ እሙን ነው፡፡ ስለሆነም፣ መሳሪያዎቻችንን ማጽዳትና ከጀርሞች ነጻ የማድረግ ልምድ የምንጊዜም ተግባራችን መሆን አለበት፡፡  

  • በተቻለ መጠን፣ ወደምንፈልገው አቅጣጫ ጠቁመን የምንይዛቸውን ፊሽፖል ማይክራፎኖችን (directional ‘fishpoles’) ለስጋት በማያጋልጥ ርቀት ሆነን እንጠቀም። የሚስኩ ማይክራፎኖችን መጠቀም የሚኖርብን፣ ሌላ አማራጭ ስናጣ ከመሆኑም ባሻገር፣ ለጤንነት/ለንጽህና የሚደረግውን ጥንቃቄ ሳናጓድል መሆን አለበት።
  • ሁሌም ከሥራ በኋላ ፣ የማይክ ሽፋኖች፣ ከጀርም መጽዳትና በፈላ ውሃና በፈሳሽ ሳሙና መታጠብ አለባቸው፡፡ ሽፋኖችን በጥንቃቄ በማውለቅ ካንዱ ወደሌላው ሊተላለፍ የሚችልን ብክለት ለመከላከል የሚያስችለንን ስልጠና/መመሪያ ከሚመለከተው አካል ጠይቀን ማግኘት አለብን፡፡ በተቻለ መጠን፣ እንደ ዊንድ መፍ (‘wind muff’) ያሉ፣ ለማጽዳት ሊያስቸግሩ የሚችሉ፣ የማይክ መሸፈኛዎችን ከመጠቀም እንቆጠብ፡፡ 
  • በተቻለ መጠን፣ ዋጋቸው ረከስ ያሉ የጆሮ ማዳመጫዎችን ተጠቅመን እንደምንጥላቸው (በተለይም እንግዶቻችን የተጠቀሙባቸውን) እናስብ፡፡ ሁሌም የጆሮ ማዳመጫዎችን ከመጠቀማችን በፊትና ከተጠቀምንባቸው በኋላ መጠራረግና ከጀርም ማጽዳታቸንን አንዘንጋ፡፡
  • ርቀታችንን ጠብቀን ያለስጋት ስራችንን መስራት የሚያስችሉንን ረጃጅም ሌንሶች እንጠቀም፡
  • በተቻለ መጠን፣ ገመድ አልባ የሆኑ ተንቀሳቃሽ መሳሪያዎችን እንጠቀም፡፡
  • ሥራችንን ስናጠናቅቅ የተጠቀምንባቸውን መሳሪያዎች በምን እግባብ ማስቀመጥ እንዳለብን እናሰተውል፡፡
  • የምንችል ከሆነ እየተጠቀምንበት ያለውን መሳሪያ ከፕላሰቲክ በተሰራ መሸፈኛ ዙሪያዉን እንጠቅልለው፡፡ ይህን በማድረጋችን፣ የመሳሪያዎችን የውጭ አካል በቫይረሱ ከመበከል እናድነዋለን፡፡ በተጨማሪም፣ መሳሪያውን በቀላሉ ለማጽዳትና ከጀርም ነጻ ለማድረግ ያስችለናል፡፡
  • በደንብ ቻርጅ የተደረጉ ተጨማሪ ባትሪዎችን በመያዝ ስራ ላይ እያለን ባትሪን ቻርጅ ከማድረግ እንቆጠብ፤ ይህንን በማድረግ መሳሪያችንን በቫይረሱ ከመበክል እናድነዋለን፡፡
  • ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ፣ እንደ ሜሊስፕቶል ያሉ ጸረ-ጀርም መጥረጊያዎችን በመጠቀም መሳሪያዎችን በሚገባ እናጽዳ አስከትሎም፣ የእጅ ስልኮችን፣ ታብሌቶችን፣ መሰኪያዎችን፣ ላፕቶፖችን፣ ሃርድ ድራይቮችን፣ ካሜራዎችን፣ የይለፍ ካርዶችንና ገመዶችን በሳኒታይዘር እናጽዳ፡፡
  • የተጠቀምንባቸውን መሳሪያዎች ወደ ቦታቸው ከመመለሳችን በፊት፣ ከብክለት ነጻ መሆናቸውን ማረጋገጥእነዚህን መሳሪያዎች የሚጠቀሙ ሌሎች ባለሙያዎችም መሳሪያዎቹን እንዴት በንጽህና የመያዝና ከብክለት ነጻ የማድረግ እውቀትና ስልጠና ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ፤ የትኛውም ዓይነት መሳሪያ እንዲያው ዝም ብሎ ያልተተወ እና ለተገቢው ሰው በአግባቡ የተመለሰ መሆኑን ማረጋገጥ
  • አንድን ተሽከርካሪ ለስራ ተጠቀመን ካበቃን በኋላ፣ የተሽከርካሪው የውስጥ አካል ሙልጭ ተደርጎ በደንብ መጸዳቱን ማረጋገጥ አለብን፤ የሚያጸዳው ሰው ተገቢውን ስልጠና የወሰደ ቢሆን ይመረጣል። ጽዳቱ ሲከናወን፣ አዘውተረው የሚነካኩ ቦታዎች ማለትም፣ የተሽከርካሪው የበር እጀታዎች፣ የማርሽ መቀየሪያዎች፣ የእጅ ፍሬን፣ መሪው፣ የጎን መስታዎቶች፣ የአንገት መደገፊያዎች፣ የተሸከርካረ ቀበቶዎች፣ ዳሽቦርዶችና ሌሎች የሚነካኩ ቁልፎች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡

የኤሌትሪክ መሳሪያዎችን ስለማጽዳት

የኤሌትሪክ መሳሪያዎችን ለማጽዳት የሚከተሉት ነጥቦች እንደ አጠቃላይ መመሪያ ሊያገለግሉን ይችላሉ። የምንጠቀምበትን አንድን መሳሪያ ለማጽዳት ክመሞከራችን በፊት፣ ሁሌም መሳሪያውን ያመረተው ድርጅት ያዘጋጀውን መመሪያ በሚገባ ማንበብ ይኖርብናል።ሁሌም የኤሌትሪክ መሳሪያዎችንና የኤሌትሪክ ገመዶችን ከሶኬቶች መንቀል/ማላቀቅ አለብን።  

  • ፈሳሸ ንገሮችን ከመሳሪያዎቻችን እናርቅ፤ መሳሪያዎቻችንን ለማጽዳት ብሊቾችን፣ የሚረጩ መርዞችን አንጥቀም። እንደዚያ ካደርግን፣ መሳሪያዎቻችን እንጎዳቸዋለን። 
  • መሳሪያዎቻችን ላይ ምንም ነገር አንርጭ።
  • መሳሪያዎቻችን ለማጽዳት ለስላሳ አና ሸካራነት የሌላችው ጨርቆችን አንጠቀም።
  • ለማጽዳት የምንጠቀምበትን ጨርቅ ትንሽ ውሀ አናስንካው አንጅ አንንከረው።
  • መሳሪያዎችንን ደግመን ድጋግመን በደንብ አንጠራርገቸወ:
  • ክፍተት ያላቸው የኤሌትሪክ መሳሪያዎች (ለምሳሌ ቻርጅ የማድረጊያ ሶኬቶች፣ የጆሮ ማዳመጫ ሶኬቶቸ፤ኪቦርዶችን) እርጠበት እንዳያገኛቸው እንጠንቀቅ።
  • መሳሪያዎችንን በንጹህ፣ በደረቅና በለስላሳ ጨርቅ እናጽዳ።
  • አንዳንድ ፋብሪካዎች ምንም ክፍተት የሌለባችውን መሳሪያዎችን ለማጽዳት የምንጠቀምበት አልኮል ክ70% በላይ የሆነ አልኮልነት (isopropyl alcohol) ሊኖረው አንደሚገባ ይምክራሉ።
  • ሁሌም መሳሪያችንን ጸረ-ጀርም ተጠቅመን ከማጽዳታችን በፊት፣ የአምራቹ ድርጅት የሚለውን ማረጋገጥ አለብን፤ አለበለዚያ፣ ጸረ-ጀርሙ መሳሪያችንን ሊጎዳብን ይችላል።

ተጨማሪ ዝርዝር መመሪያዎችን ደግሞ እዚህ መጣጥፍ ዘንድ ማግኘት ይቻላል።

የዲጂታል ደህንነት

  • ስለ ኮቪድ-19 ቫይረስ ስርጭት የምንዘግብ እኛ ጋዜጠኞች የኢንተርኔት ጥቃት እንደሚያጋጥመን ልንገነዘብ ይገባል። ጥቃቱም ከፀረ-ክትባት ቡድኖች ወይም የፊትና የአፍንጫ ጭንብሎችን ማድረግ ከሚቃወሙ ወገኖች ሊቃጣ ይችላል። እራሳችንን  ከጥቃት ለመከላከል በሲ.ፒ.ጄ የተሰነደውን መልካም ተሞክሮ በጥንቃቄ በመመርመር ራሳችንን ከጥቃት እንታደግ፡፡ 
  • የኮቪድ-19ን ስርጭት ለመከታተል፣ መንግስታትና የቴክኖሎጂ ድርጅቶች በየጊዜው ቅኝቶችን ያደርጋሉ፡፡ ሲትዝን ላብ (Citizen Lab)እንደሚለው፣ ይህ ቅኝት በፒጋሰስ (Peagasus) የተሰራውን ኤን.ኤስ.ኦ ቡድን (NSO Group) ይጨምራል። ሥራውም ጋዜጠኞችን ኢላማ ባደረጉ የስለላ መረቦችን (Spyware) መከታተል ነው፡፡ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል (Tranasparency Internantional) የተስኘው ተቋም እነዚህን ሂደቶች እየተከታተለ በድህረ ገፁ ያሰፍራል፡፡
  • ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የጤና ቀውስ ተጠቅመው፣ ወንጀለኞች፣ ከክትባቱ መጀመር ጋር ቁርኝት ያላቸውን ግለስቦችን እና ድርጆቶችን የማጥመድ ነገር እየተለመደ መጥቷል። ከኮቪድ-19 ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ወይም ክትባቶችን የያዙ ሊንኮችን ከመጫናችን ወይም ከማውረዳችን በፊት፣ ቆም ብለን በአንከሮ ማስብ ይኖርብናል፡፡ ኤሌክጽሮኒክ ፍሮንጻየር ፋንዴሽን (Electronic Frontier Foundation) ጥናት እንደሚያሳየው፣ የጥቃታቸው ደረጃም የተወሳሰቡ የኢንተርኔት የማጥቂያ ዘዴዎችን  በመጠቀም የእኛን የጋዜጠኞችን መሳሪዎች እስከ ማኮላሸት ደርሷል፡፡ ኮቪድ-19ን በተመለከተ መረጃ የሚሰጡ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ወይንም መልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎችን (messaging apps) ከመጫናችን በፊት፣ ኮምፒውተሮቻችንን ሊያጠቁ ወደሚችሉ አደገኛ ቫይረሶች  (malware) ሊያገናኙን እንደሚችሉ አውቀን ጥንቃቄ አናድርግ፡፡
  • በጋርዲያን (The Guardian) እንደተዘገበው፣ በመንግስት የታገዘ የሀሰት መረጃ እንዳለ ልንገነዘብ ይገባል። እንደዚህ ያለውን አጠቃላይ የሀሰት መረጃ በተመለከተ፣ የአለም ጤና ድርጅት ጥንቃቄ እንዲደረግበት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ቢ.ቢ.ሲም በቂ ማስገንዘቢያ አለው፡፡ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ድባቅ መምቻ (myth buster) መመሪያም በአለም ጤና ድርጅት ድህረ-ገጽ ላይ ይገኛል፡፡
  • በመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች አማካኝነት የሚተላለፉ ሀሰተኛ ዜኛዎችና አሳሳች መረጃዎችም እንዳሉ ልናውቅ ይገባል፡፡
  • ፌስቡክ ላይ የሚገኙ አንዳንድ የኮቪድ መልክቶች፣በሰዎች ፋንታበአርቴፊሻል ኢንተሌጀንስ አማካኝነት እየተቀነባበሩ እንደሚሰራጩ ተደርሶበታል፤ እንዲያውም፣ ተገቢነት ያላቸው መልክቶች ስህተት (error)ተብለው እሰከ መፈረጅ ደርሰዋል፡፡
  • በኢንተርኔት ኮንፈርንሶች እና በግል ኑሮ ጉዳዮች (privacy issues) ዙሪያ የተጻፉ ፅሁፎችን እናንብብ፤ ይህንን ስናደርግ፣ እነዚህ አገልግሎቶች መረጃዎቻችን ላይ ምን እንደሚፈጽሙ፣ የትኞችን መረጃዎች ማግኘት እንደሚችሉ፣ ከአደጋ ነጻ የሆኑ መረጃዎች የትኞቹ  እንደሆኑ ለማወቅ የሚያስችል ግንዛቤ ይኖረናል፡፡ ባሁኑ ጊዜ በርካታ ሰዎች  ስራቸውን እቤታቸው ሆነው በማከናወን ላይ ይገኛሉ፤ ይህንንም ተከትሎ፣ ብዙዎቹ የኢንተርኔት መንታፊዎች ኢላማ እየሆኑ እንደመጡ ልብ ልንል ይገባል፡፡
  • በአምባገነን መንግስታት በሚመሩ አገሮች ውስጥ ስለኮቪድ-19 ስርጭት መዘገብ አደጋ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ መንግስታት አዘጋገቡን በአንክሮ ይከታተሉታል፡፡ በሲ.ፒ.ጄ እንደተለገጸው፣ አንዳንድ መንግስታት፣የቫይረሱን ስርጭት መጠን ለመሸሸግ በሚያደርጉት ጥረት፣ ሚዲያውን ሳንሱር እስከ ማድረግ ይደርሳሉ፡፡

ወንጀል እና በሥራ ላይ ስለሚደረግ አካላዊ ጥንቃቄ

  • እኛ ጋዜጠኞች ዓለማቀፋዊ የዘገባ ሥራ ለመስራት መጓዝ የምንችል ከሆነ (ከታች እንደታየው) ፣ ስለምንሄድበት ቦታ የፀጥታ ሁኔታ አስቀድመን ጥናት ማካሄድ ይኖርብናል፡፡ ወረርሽኙ ከተክሰተ አንስቶ አስከፊ ግጭቶችና ተቃውሞዎች እዚህም እዚያም ተከስተዋል፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞች እንደተሰደቡና የወንጀል ኢላማ እንደሆኑ እየተናገሩ ስለሆነ፣ የደህንነት ስጋት አይኖርብኝም በሚል መዘናጋት የለብንም።
  • በተለይ ከገጠራማ ቦታዎች ስንዘግብ ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ በሽታውን ሊያመጡብን ይችላሉ በሚል ስጋት፣ ሰዎች በ‘መጤዎች’ ላይ የጥርጣሬ ወይንም የጠላትነት ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል፡፡
  • ከኮቬድ 19 በተያያዘ፣ ከቤት ያለመውጣት ድንጋጌዎችን ተከተሎ፣ በተለያዩ ሀገራት በፖለስ በኩል፣ የድብደባ ስጋቶችን ጨምሮ ጠንካራ እርምጃወች እየተወሰዱ እንዳሉ ልብ ልንል ይገባል፡፡
  • በሲ.ፒ.ጄ እንደ ተገለጸው፣ በአምባገነን ሥርዓት በሚተዳደሩ ሀገሮች የሚሰሩ ጋዜጠኞች ስለኮቪድ-19 ስርጭት  በሚዘግቡበት ጊዜ የመታሰር አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል በንቃት ሊከታተሉ ይገባል፡፡

የውጭ ጉዞን ያካተቱ ሥራዎች

በመላው ዓለም በተደነገጉ የጉዞ እቀባዎች የተነሳ፣ በአሁኑ ሰዓት የውጭ ጉዞዎች እጅግ እየቀነሱና በጣም አዳጋች እየሆኑ ቀጥለዋል፡፡ 

  • ከአገር ውጭ ወጥተን የዘገባ ሥራ የምንሰራ ከሆነ የሚከተሉትን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብናል፤
  • ከቤት ያለመውጣትና የሰአት እላፊ ገደቦች በተለያዩ ሀገራት ሊለያዩ እንደሚችሉ ልብ እንበል፤ ይሄም ሁኔታ ያለበቂ ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ ሊቀየር ይችላል። ስለሆነም፣ በምንሄድበት ሀገር ሊወጡ ስለሚችሉ የእንቅስቃሴ ክልከላዎች/ገደቦች ያካባቢውን የዜና ምንጮች በአንክሮ እንከታተል።
  •  ሰዎችን ወደ ለይቶ ማቆያ ቦታዎች የመውሰድ እርምጃዎች፣ ተመልሰን ለስራ እንደምንመጣበት ያካባቢ ሁኒታ፣ ያለበቂ ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ፣ በአዲስ መልክ ሊውጡ/ሊሻሻሉ ይችላሉ።
  • የጤና ባለሙያዎች በጥቂት ወይም ያለምንም ማስጠንቀቂያ የስራ መቆም አድማ ሊመቱ አንደሚችሉ በመግንዝብ፣ ለዘገባ ስራ በተሰማራንበት ቦታ የሚገኙትን የህከምና መስጫ ተቋማት ሁሉ ለይተን ማወቅ አለብን፡፡ 
  • ራስን ለመከላከል የሚያገለግሉ መሳሪያዎች እንደልብ ላይገኙ፣ ከነአካቴው ላይኖሩ ወይንም የጥራት ደረጃቸው አጠረጣሪ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም፣ ሁሌም ለስራ ከመሰማራታችን በፊት  የመሳሪያዎቹ መኖር አለመኖር በተመለከተ ጥናት ማካሄድና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ቁሳቁሶችን ይዞ መሄድ ያስፈልጋል፡፡
  • አንድ ቦታ ለስራ ከመሄዳችን በፊት፣ የምንችል ከሆነ የኮቪድ ክትባት መውስድ ይኖርብናለ፤ በደህናው ጊዜ ልንጠየቃቸው የሚችሉ አስፈላጊ የክትባት አይነቶችን አሟልትን መያዛችንን ማረጋገጥ ተገቢ ነው። 
  • ስለጉዟችን የጉዞ የመድን ዋስትና መግዛት ይኖርብናል፤ ብዙ መንግስታት፣ የውጭ ጉዞን በተመለከተ የተለያዩ የጉዞ ምክሮችንና ማስጠንቀቂያዎችን እንዳወጡ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ኮቪድ-19ን ለመዘገብ ለሚደረግ ጉዞ፣ የኢንሹራንሱ ሽፋን ላይሰጡ እንደሚችሉ ልብ ልንል ይገባል፡፡ 
  • ልንዘግበው ስለአሰብነውን ሁነት ስናቅድ፣ ብዙ ሃገራት ስለአሰተላለፏቸው ህዝባዊ ስብሰባን ሰለሚከልክሉ ድንጋጌዎች መከታተል አለብን፤ እስከ ምን የህል ቁጥር አንድ ላይ መሆን እንደተፈቀድም እንደዚሁ ማወቅ ተገቢ ነው፡፡
  • በብዙ የዓለማችን ክፍል፣ የየብስ ድንበሮች እንደተዘጉ ናቸው፡፡ ክፍት ሆነው የቆዩ የትኞቹም ደንበሮች ያለምንም ማስጠንቀቂያ መልሰው ሊዘጉ ሰለሚችሉ፣ የድንገተኛ ጊዜ አማራጭ እቅዶቻችን ይህንኑ ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል።
  • ከታመምን አንጓዝ፡፡ ብዙዎች የአለም ዓቀፍና አየር ማረፊያዎች፣ ታላላቅ የመጓጓዣ ቀጠናዎችን ጨምሮ፣ ጠንካራ የጉዞ የምርመራ ሥርዓቶችን በስራ ላይ አውለዋል፡፡ በርካታ ተመርማሪ መንገደኞች በእርግጠኝነት ወደ ማግለያ ቦታ ሊወሰዱ ወይም እራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩ ሊደረጉ ይችላሉ፡፡
  • አዳዲስ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ ኮቪድ-19፣ በብዙ አየር መንገዶች ታላቅ የገንዘብ ኪሳራ አድርሷል፡፡ ስለዚህ፣ የጉዞ ትኬቶች ስንገዛ፣ ጉዟችን ቢሰረዝ፣ ገንዘባችን ሙሉ በሙሉ ተመላሽ እንደሚሆን ማረጋገጥ አለብን፡፡
  • በጣም ብዙ ሀግሮች ቪዛ መስጠት አቁመዋል፣ የሰጡትንም ቪዛ ስራ ላይ እንዳይውል ያደረጉ አሉ፡፡ ስለሆነም፣ የምንሄድበትን ሀገር የቪዛ ሁኔታ አስቀድሞ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡
  • የምንሄድበት ሀገር ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናችንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ወረቀት ማቅረብ እንደሚያስፈልገን ወይም እንደማያስፈልገን አስቀድመን ማረጋገጥ አለብን፡፡ 
  • በብዙ የአየር መንገድ ኬላዎች፣ የጤና ምርመራ እርምጃዎች እና የሙቀት መለኪያዎች ይከናወናሉ፡፡ በመሆኑም፣ የበረራ ፕሮግራማችን እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት፤ የበረራ ዕቅዳችንን ተለማጭ (Flexible) ማድረግ ይኖርብናል፡፡ በባቡር፣ በመርከብ ወይንም በአገር አቋራጭ አውቶብሶች ስንጓጓዝም፣ ተመሳሳይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል፡፡

ሥራችንን ከጨረስን በኋላ

  • ሊከሰቱ የሚችሉ የህመም ምልክቶችን ልብ ማለት እና የጤንነታችንን ሁኔታ አዘውትሮ መከታተል፡፡
  • ለአደጋ በከፍትኛ ደረጃ ከተጋለጠ የዘገባ ስራ መልስ፣ እራሳችንን አግልለን መቆየት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚሰጡትንም ምክር ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡
  • ስለ ኮቪድ-19 የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን መከታተል አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ደግሞ፣ ስለነበርንበትና ስለመጣንበት ሀገር እየተተገበሩ ስላሉ ሙሉ በሙሉ የማግለል ስርዓቶችን ይጨምራል፡፡
  • ያለንበት ሀገር የቫይረሱ የወረርሽኝ ሁኔታን መሰረት በማድረግ፣ ከነበርንበት ቦታ ከተመለስን በኋላ ላለፉት 14 ቀናት ከእነማን ጋርና ከምን ያህል ሰው ጋር እንደተገናኝን ማስታወሻ መያዝ አለብን፡፡ ይህን ማድረግ ምናልባት የቫይረሱ ምልክት ከታየብን፣ የአገኘናቸውን ሰዎች በቀላሉ አፈላልጎ ለማግኝት ይረዳል፡፡

ምልክቶች ሲታዩብን፤

  • የኮቪድ-19 ምልክቶች ከታዩብንምልክቶቹ አነስተኛ ቢሆኑም እንኳ ፣ ከአለቆቻችን ጋር ስለሁኔታው በመነጋገር፣ ሥራችንን ካጠናቀቅንበት ቦታ በተገቢው የመጓጓዣ ዘዴ ወደ ቤታችን መመልስ አለብን። እንደ አገኘን ታክሲ መጠቀም የለብንም፡፡
  • ራሳችንና ማህበረሰባችን ለመጠበቅ፣ በአለም ጤና ድርጅትበሲ.ዲ. ሲእና በየአካባቢው የጤና ባለስልጣናት የሚሰጡ ምክሮችን እንከታተል፡፡
  • ምልክት ከታየብን ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ ለ7 ቀናት ቤታችንን ለቀን አንውጣ (እቤታችን የምንቆይበት ትክክለኛ የጊዜ ርዝመት መንግስት በሚስጠው ማሳሰቢያ መሰረት ካሀገር ሀገር ሊለያይ ይችላል) ። እንዲያ በማድረጋችን ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው ባለማስተላለፍ ማህበረሰባችንን እንጠብቃለን፡፡
  • አስቀድመን በማቀድ ከሌሎች እርዳታ እንጠይቅ፡፡ ምን ምን አቅርቦቶች እንደሚያስፈልጉን ለቀጣሪያችን፣ ለጓደኞቻችን እና ለቤተሰቦቻችን ነግረን፣ በራፋችን ላይ እንዲያስቀምጡልን 

እናድርግ፡፡

  • የምንኖርበትን ቤት ከሌሎች ሰዎች ጋር መጋራት ግድ ከሆነ፣ የተጋሩን ሰዎች ራሳቸውን ለተወሰነ ጊዜ ማግለል አለባቸው፡፡ ይህንን በተመለከተ ጠቃሚ መመሪያ እዚህ ይገኛል፡፡ ቫይረሱን ከአንዱ ወደ ሌላው ላለማስተላለፍ፣ በመታጠቢያ ቤት፣ በመፀዳጃ ቤት፣ በወጥ ቤት እቃዎች አጠቃቀም ዙሪያ የተለየ ጥንቃቄ እናድርግ፡፡
  • በተቻለ መጠን ቤታችን ውስጥ ካሉ ሰዎች ርቀታችንን ለአደጋ በማያጋልጥ መልክ እንጠብቅ፤ ማድረግ የምንችል ከሆነ፣ ለብቻችን እንተኛ፡፡

የሲ.ፒ.ጄ  የጥንቃቄ “ኪት” ለጋዜጠኞችና ለዜና ሰዎች ስለ አካላዊ፣ ዲጂታላዊ ስነ-ልቦናዊ ጥንቃቄዎች መረጃዎችና ጠቃሚ ምክሮችን ይሰጣል፡፡ ይህ ደግሞ ስለ ምርጫና ሊከሰቱ ስለሚችሉ ህዝባዊ አመጾች ተፈላጊ መረጃን ይጨምራል፡፡