መስከረም 16 2013 ዓ.ም የፕሬዝደንታዊ የምርጫ ውጤትን በመቃወም፣ የተቃዋሚ ሰልፈኞች ወደ አደባባይ በወጡ ጊዜ፣ የፖሊስ መኮንኖች አንድ የፎቶ ጋዜጠኛን ሲያስሩ:: በ2012 ዓ.ም ባለስልጣናቱ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞችን ከማስራቸውም በላይ ሌሎች በርካታ ጋዜጠኞች ላይ አስተዳዳራዊ እስራትና ቅጣት እንዲጣልባቸው አድርገዋል። (ኤ.ፒ./ቲ.ዩ.ቲ.ቢይ)

በዓለማቀፍ ደረጃ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን የጋዜጠኞች መታሰር

በ2013 ዓ.ም የታሰሩት ጋዜጠኞች ቁጥር ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን አሻቅቧል። ይህም የሆነው፣ ጋዜጠኞች ስለ ኮቪድ-19 ወረርሺኝ ሽፋን ሲሰጡ ወይም ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ሲዘግቡ፣ መንግስታት በሚያደርሱባቸው ማዋከብና ጫና ነው። ከአሜሪካ በኩል የሚሰማው የፀረ-ፕሬስ ዘመቻ፣ ዛሬም ለአምባገነኖች ከለላ ሆኗችዋል።  የሲ.ፒ.ጄ ልዩ ዘገባ በኤላና ቤይዘር 

ታህሳስ 6፣ 2013 ታተመ

ኒዮርክ

ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን፣ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሺኝ ወይንም ስለ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሲዘግቡ የነበሩ ጋዜጠኞች፣ ሥራቸውን በመስራታቸው ብቻ በዓለማቀፍ ደረጃ በአምባገነን መንግስታት ታስረዋል። በወረርሺኙ ጊዜ፣ መንግስታት የጋዜጠኞቹን የፍርድ ሂደት አጓትተዋል፤ እስር ቤት ውስጥ በበቂ ሁኔታ እንዳይጠየቁ አድርገዋል፤ እስር ቤት እያሉም ጤንነታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ሊያጋልጡ የሚችሉ ሁኔታዎችን እያዩ ቸላ ብለዋል። በዚህም የተነሳ፣ ቢያንስ ሁለት ጋዜጠኞች እስር ቤት እያሉ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ተይዘው ለሞት ተዳርገዋል::

የጋዜጠኞች ጥበቃ ድርጅት (ሲ.ፒ.ጄ) ያደረገው አመታዊ የዓለማቀፍ የጥናት ዳሰሳ እንደሚያሳየው፣ እስከ ህዳር 22፣ 2013 ዓ.ም. ድረስ ቢያንስ 274 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል። ይህም በ2009 በቻይና ተመዝግቦ ከነበረው የ272 የእስረኞች ቁጥር ይበልጣል። ይህም በ2009 ከተመዘገበው የ272 ጋዜጠኞች እስር ይልቃል፡፡ ቻይና፣ ኮቪድ-19 ወረርሺኙን የሚዘግቡ አያሌ ጋዜጠኞችን በማሰር ለተከታታይ ሁለተኛ አመት ብዙ ጋዜጠኞችን አሳሪ አገር በመሆን ተመዝግባለች። ቱርክ በዋስ የተፈቱ ጋዜጠኞችን ፍርድ ቤት ቤት በማቅረብ እንዲሁም አዳዲሶችን በማሰር አስራ ቻይናን ተከትላ ትገኛለች፡፡ ከዚያ በመቀጠል ደግሞ፣ በምንም ወንጀል ሳይከሰሱ ጋዜጠኞችን እስር ቤት የምታጉረዋ ሀገር ግብጽ ናት። ጋዜጠኞችን በማሰር፣ ግብጽን ተከትላ የምትመጣዋ ደግሞ ሳውዲ አረቢያ ናት። የሚታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ የመጣባቸው ሌሎች ሀገራት ደግሞ ቤላሩስ እና ኢትዮጵያ ናቸው። በቤላሩስ የታሳሪ ጋዜጠኞች ቁጥር የጨመረው፣ ለረጅም ጊዜ በስልጣን የቆዩትን ፕሬዝዳንት በድጋሚ መመረጥ ተከትሎ በተነሳ ተቃዋሞ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ በፖለቲካዊ ብጥብጥ ጀምሮ ወደ ጦርነት ባመራው ግጭት ምክንያት ነው። 

ይህ ሁኔታ ጨቋኝ መንግስታት ለአምስተኛ ተከታታይ አመታት፣ ቢያንስ 250 ጋዜጠኞችን እንዳሰሩ ያመለክታል። የዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ለማስጠበቅ የሚደረግ ዓለማቀፋዊ አመራር እጦት፣ በተለይ ከአሜሪካ ይገኝ የነበረውን የመሪነት ሚና መቅረት ተከትሎ፣ ችግሩ በጣም ተባብሶ ቀጥሏል። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የጋዜጠኝነት ስራን ያለመታከት በማንቋሸሻቸውና እንደ ግብጽ ፕሬዝደንት አብደል ፋታ አል-ሲሲ ያሉ አምባገነኖች  የልብ ወዳጅነት በመመስረት ችግሩ እንዲባባስ አድርገዋል። “ሐሰተኛ ዜና” የሚለውን የትራምፕ ዲስኩር በማቀንቀን ብዙ አምባገነኖች፣ በተለይ በግብጽ፣ “የሐሰተኛ ዜናን” በማስራጨት ሰበብ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር በየጊዜው በገፍ እንዲጨምር አድርገዋል። በዚህ አመት 34 ጋዜጠኞች “የሐሰተኛ ዜና” በማቅረብ ሰበብ ለእስር ተዳርገዋል። ባለፈው አመት የታሰሩት ጋዜጠኞች ቁጥር 31 ነበር።

አሜሪካ ውስጥ ሲ.ፒ.ጄ ታሳሪ ጋዜጠኞን ቆጠራ ባደረገበት ወቅት፣ አንድም ጋዜጠኞች በእስር ላይ አልነበረም። ይሁን እንጂ፣ የአሜሪካው የጋዜጠኝነት መብት ተከታታየ እንዳመላከተው፣ እስካሁን ባልተለመደ መልኩ፣ በ2013 ዓ.ም. 110 ጋዜጠኞች ለእስር የተዳረጉ ወይም በወንጀል የተከሰሱ ሲሆን፣ 300 የሚሆኑት ደግሞ በሕግ አስከባሪዎች ውክቢያ ተፈጽሞባቸዋል። ቢያንስ 12 የሚሆኑት ደግሞ፣ አሁንም የወንጀል ክስ ቀርቦባቸው የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከፊሎቹ ክሶች የእስር ቅጣትን አዝለዋል፡፡ ታዛቢዎች ለሲ.ፒ.ጂ እንደነገሩት፣ ከፋፋይ የሆነው የፖለቲካ ምሕዳር፣ ወታደራዊ ሕግ የማስከበር ስርዓት፣ በተለያዩ ጊዚያት በሚደረጉ የተቃዋሞ ሰልፎች እና በጋዜጠኞች ላይ የሚስነዘሩ የጥላቻ ንግግሮች በአንድ ላይ ተዳምረው ጋዜጠኞች ከዚህ በፊት ያገኙት የነበሩትን የፖሊስ የሕግ ከለላ እንዲያጡ አድርጓቸዋል።

የአሜሪካ ዓለማቀፋዊ የፕሬስ ነጻነት የመሪነት ሚና ስለሚያንሰራራበት ሁኔታ፣ ሲ.ፒ.ጄ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ባይደን ምክረ-ሀሳቦችን አቅርቧል። ከተካተቱት ምክር-ሐሳቦች መሀል፣ በየቦታው በጋዜጠኝነት ላይ ስለሚቃጡ ጥቃቶች ኃላፊነት መውሰድንና በውጭ ሀገር የተመደቡ ዲፕሎማቶች የተከሰሱ ጋዜጠኞችን የፍርድ ሂደት እንዲከታተሉ ማዘዝን እና ስለ ግሉ ሚድያ መብት መቆምና ድጋፍ መስጠት ይገኙብታል።  ሲ.ፒ.ጄ በአሜሪካ በሚድያ ላይ የአመኔታ እጦት በተለይም በዓለማቀፉ ወረርሺኝ ጊዜ አስከፊ ደርጃ ላይ እንደደረሰ አመልክቷል

ኦሪጎን፣ ፖርትላንድ ውስጥ፣ ነሃሴ 24 2012 ዓ.ም ለተቃዋሞ የወጡ ሰልፈኞች እንዲበተኑ በተደረገ ጊዜ አንድ የኦሪጎን ግዛት ወታደር ጋዜጠኛ ጋብርኤል ትረምብሊን ሲያስር። በአሜሪካ በ2012 ዓ.ም ከ100 በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ታስረዋል ወይም ክስ ተመስርቶባቸዋል። (የጌቲ ምስሎች/ኤ.ኤፍ.ፒ/ ናታ ሆዋርድ)

ቻይና ውስጥ ከታሰሩት 47 ጋዜጠኞች መሀል፣ ብዙዎቹ ለረጅም ጊዜ በእስር የቆዩ ወይም በዢንጄያንግ ክፍለ ሀገር ለምን እንደታሰሩ እንኳ ሳይገልጽ ለእስር የተዳረጉ ናቸው። በያዝነው አመት መጀመርያ፣ የኮሮናቫይረስ በሁቤይ ግዛት የምትገኘውን የውሀን ከተማ ቁም ስቅሏን ባሳያት ጊዜ፣ ከቤጂንግ መንግስታዊ ምላሽ በተቃራኒ የሚዘግቡ አያሌ ጋዜጠኞች ታስረዋል። እስከ ህዳር 22። 2013 በእስር ላይ ከሚገኙ ሶስት ጋዜጠኞች መካከል፣ ከየካቲት መጀመሪያ አንስቶ ከውሀን ዘገባዎችን ትዊተር እና ዩቱዩብ ላይ ትለጥፍ የነበረውችውና ግንቦት 14 የታሰረችው የቪድዮ ጋዜጠኛ ዝሃንግ ዝሃን ትገኝበታለች። ቪድዮዎቹም የኮቪድ-19 ያስከተለውን ተጽዕኖ እና ወረርሺኙን ለመቆጣጠር በመንግስት እየተውሰድ ያለውን እርምጃ በተመለከተ ከንግዱ ማህበረሰብ እና ከሰራተኞቹ ጋር የተደረጉ ቃለመጠይቆችን አካተዋል።

በመንግስት ደረጃ ሳንሱር እንደሚደረግባቸው ወይም ቁጥጥር እንደሚካሄድባቸው ሲገነዘቡ፣ ማህበራዊ ድህረ ገጾችን በዋናነት እንደሚጠቀሙ ሲ.ፒ.ጄ ለይቶ ካወቃቸው በደርዘን ከሚቆጠሩ ጋዜጠኞች አንዷ ዝሃንግ ዝሃን ናት። እነዚህ ቪድዮዎች ከቻይና ውጭ ባሉ ድርጅቶች ስለሚስተናግዱ፣ እስከ አሁን ድረስ ለዓለማቀፉ ሕብረተሰብ ተደራሽ እንደሚሆኑ ይገመታል። ይሁንና፣ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውና በሌሎች ጋዜጠኞች የተዘጋጁ ሥራዎች በግልጽ ባልታወቁ ምክንያቶች ከድረ-ገጾች እንዲወርዱ ተደርገዋል። ይህ ሁኔታም፣ ለጥናትና ምርምር እንቅፋት እንደሚሆንና፣ ጉግል፣ ትዊተር እና ፌስቡክ በመሳሰሉ ታላላቅ የቴክኖሎጂ ተቋማት የአስራር ግልጽነት ላይ ጥያቄ እንደሚያጭር እሙን ነው።

ከዚህ በተጨማሪም፣ ቻይና ውስጥ ለተለያዩ የአሜሪካ የህትመት ሥራዎች የሚሰሩ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞችን በተባረሩበት ዓመት  ዲፕሎማሲያዊ እሰጣ አገባዎችን ተከትሎ የውጭ ሚዲያ ተቃማት አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል  ። በመንግስት ባለቤትነት ለሚተዳደረው የቻይና አለም አቀፋዊ ቴሌቪዥን ኔትወርክ የምትሰራውና ንግድ ነክ ጉዳዮችን የምትዘግበው የአውስትራሊያ ዜግነት ያላት ቼንግ ሌይ፣ በአውስትራሊያ እና በቻይና መካከል የተከሰተውን ውዝግብ ተከትሎ የሀገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ ጥላለች በሚል ክስ ለእስር ተዳርጋለች። ይህም፣ በስለላ ተከሶ ከጥር 2011 ጀምሮ በእስር የሚገኘውን የኢንተርኔት ጋዜጠኛ ያንግ ሄንግጁን ተከትሎ፣ ሁለተኛዋ የአውስትራሊያ ታሳሪ ጋዜጠኛ አድርጓታል። 

ይህ ከዩቱበ የተነሳው ‘ስክሪንሾት’ የሚያሳየው ዝሃንግ ዝሃን የተባለችው በግሏ የምትሰራ የቪድዮ ጋዜጠኛ በሁቤይ ክፍለሃገር ውሀን ውስጥ ከሚገኝ የባቡር ጣብያ አጠገብ በመዘገብ ላይ እያለች ነው። ቪዲዮው የተጫነው፣ ጋዜጠኛዋ ስለ ኮቪድ-19 ወረርሺኝና የቻይና መንግስት ወረርሺኙን ለመቆጣጠር እየወሰደ ባለው እርምጃ ስለደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጫና በመዘገቧ፣ ከታሰረችበት ግንቦት 6 2012 ዓ.ም አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የግብጽ ባለስልጣናት፣ ጋዜጠኞችን በግፍ ማሰርን፣ መክሰስን፣ ከሕግ ውጭ ማሰርን አጧጡፈውታል። በመሆኑም፣ በሀገሪቱ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ቁጥር 27 ከመድረሱም  በላይ በ2008ዓ.ም የተመዝገብውን የምንጊዜም ከፍተኛ ቁጥር ተስተካክሎታል። ህዳር ወር ውስጥ ብቻ፣ አቃቤ-ህግ፣ ሰይድ አብድ ኢላህ በተባለ የፎቶግራፍ አንሽ እና ሞሃመድ “ኦክሲጅን” ኢብርሃም በተባለ የድህረ-ገጽ ጋዜጠኛ ላይ አዲስ  የሽብርተኝነት ክስ በመመስረት፣ ጋዜጠኞቹ ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዳይተገበር አድርጓል። ሲ.ፒ.ጄ እንደዘገበው፣ የግብጽ ባለስልጣናት፣ ተመሳሳይ ዘዴዎችን በመጠቀመ ቢያንስ ስምንት የሚሆኑ የሌሎች ጋዜጠኞች የእስራት ጊዜ እንዲራዘም አድርገዋል።

በዚህ አመት፣ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያትና ወረርሺኙን ግምት ውስጥ ባላስገባ ሁኔታ፣ ግብጽ ውስጥ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ቀጥሏል። በተለይ በአንድ አጋጣሚ የተፈጸመው ድርጊት በጣም ሞትን አስከትሏል ። ከኮቪድ-19 ወረርሺኝ የዘገባ ሥራቸው ጋር በተያያዘ፣ በቫይረሱ ተጠቅተው ስለመጡ ሐኪሞች እና ነርሶች የመንግስት የዜና አውታሮች በቂ ሽፋን አልሰጡም ብለው በመተቸታቸው፣ ቢያንስ ሶስት ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል። የቤተሰብ አባላትና የህግ ጠበቆችን ጨምሮ፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጎብኚዎች ወደ እስር ቤት እንዳይመጡ ክልከላ አድርጓል፤ ለዚህም ወረርሺኙን እንደ ሰበብ ተጠቅሞበታል።

ያም ሆኖ፣ የግብጽ መንግስት የደህንነት መኮንኖች፣ በኮቪድ-19 በመያዙ የተነሳ እራሱን አግልሎ የተቀመጠውን ሳደድ ስሃታን፣ ነሃሴ 24 ቀን ይዘው አስረውታል። ፖሊስ ጣብያ እንደደረሰም፣ ራሱን ስለሳተ፣ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ እጁን በካቴና ተጠፍሮ በጽኑ ህሙማን ክፍል እንዲቆይ ተደርጓል። ከሁሉም በላይ አስከፊ እጣ ፈንታ የገጠመው ግን፣ ሃማድ ሙኒር ነው። የኮቪድ-19ኝን ለመከላከል መንግስት በወሰደው እርምጃ ላይ ይህ አንጋፋ ጋዜጠኛ ያቀረበውን ትችት ተከትሎ፣(ለአልጀዚራ ግንቦት 16 የሰጠውን ቃለ መጠይቅ፤ ለሰኔ 7 አምድ ያቀረበውን ጽሁፍ ጨምሮ ማለት ነው)፣ ሰኔ 8 እንዲታሰር ተደርጓል። የቀረበበት ክስ  ደግሞ፣ የአሸባሪ ቡድን አባል መሆን፣ የውሸት ዜናዎችን ማሰራጨት እና የማህበረሰብ ትስስሮችን አላግባብ መጠቀም ናቸው። ካይሮ በሚገኘው የቶራ ወህኒ ቤት እያለ፣ በጽኑ በመታመሙ ሰኔ 25 ከእስር ተፈቶ፣ ጊዛ ሆስፒታል ውስጥ በኮቪድ-19  ሳቢያ በተፈጠረ ከፍተኛ የጤና መታወክ ሀምሌ 6 ቀን ሞቷል፡፡

የግብጽ መንግስት የማስታወቂያ አገልግሎት ባዘጋጀው የጉብኝት መርሃግብር ከመናገሻ ከተማዋ ካይሮ ዳርቻ በስተደቡብ በሚገኝ የእስር ቤት ማማ አጠገብ አንድ ግብጻዊ ፖሊስ በጥበቃ ላይ እያለ የሚያሳይ ፎቶ። ቶራ እስር ቤት እያለ በኮቪድ-19 ተይዞ በመታመሙ ቢያንስ አንድ እስረኛ ህይወቱ አልፏል። (ኤ.ኤፍ.ፒ/ክሃሌድ)

በዓለማቀፍ ደረጃ፣ ቢያንስ አንድ ሌላ ጋዜጠኛ እስር ቤት እያለ በኮቪድ-19 በመያዙ ምክንያት ሞቷል፡፡ ይህ ጋዜጠኛ፣ ዴቪድ ግሎቦ ርሜር የተባለው የሬድዮ ግሎቦ እና የግሎቦ ቲቪ ዳይሬክተር ነበር። ይህ ጋዜጠኛ የሞተው ሀምሌ 11፣ 2012 ዓ.ም በዋና ከተማዋ ቴጉሲጋልፓ አጠገብ በታማራ በሚገኝ እስር ቤት ሲሆን፣ ለሞቱም ምክንያት የሆነው  የቀድሞ አቃቤ ሕግን ሥም አጥፍተሃል ተብሎ አስር አመት ተፈርዶበት በእስር እያለ በኮቪድ-19 በመያዙ ነው። ይህን በእስር ላይ እያሉ ለቫይረሱ የመጋለጥን አደጋ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሲ.ፒ.ጄ ከሌሎች 190 ቡድኖች ጋር በመተባበር #ጋዜጠኝነትንነጻእናውጣ በሚል ዘመቻ አማካይነት ለዓለም መሪዎች የታስሩ ጋዜጠኞች ሁሉ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርቧል። 

አዚምጆን አስካሮቭ የተባለው የ ዓለማቀፍ የጋዜጠኛ ነጻነት ተሸላሚ እስር ቤት እያለ ነው በ2012 ህይወቱ ያለፈው። ይህም የሆነው፣ የኪጊዝ ባለስልጣናት ጋዜጠኛውን እንዲፈቱ የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ፣ ሲ.ፒ.ጄ እና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች አመታትን የፈጀ ዘመቻ እያደረጉ ባላበት ሁኔታ ነበር። የእድሜ ልክ ተፈርዶበት የነበረው አስካሮቭ  የተከሰሰው ፖሊስ በድሎኛል ብሎ በማጋለጡ የተነሳ በቂም በቀል በተፈበረከ የፈጠራ ክስ ነበር። ክሃዲቻ አስካሮቭ የተባለችው የጋዜጠኛው ሚስት ለሲ.ፒ.ጄ እንደተናገረችው ከመሞቱ ሳምንታት ቀደም ብሎ፣ እስካይሮቭ መራመድ ካለመቻሉም በላይ ከፍተኛ ትኩሳት ነበረው። የእስር ቤቱ አመራር ምርመራ ባያደርግለትም ቅሉ፣ አስካሮቭ በኮቪድ-19 ተይዞ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬዋን ገልጻለች።

በሌላው የአውሮፓ ክፍል እና በመካከለኛው እስያም፣ በቤላሩስ፣ በተነሳ ብጥብጥ ጋዜጠኞች ችግር ገጥሟቸዋል። የተጭበረበረ ምርጫ ነው ተብሎ በስፋት በሚታመንበት ምርጫ፣ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሽንኮ ለስድስተኛ የስልጣን ዘመን አሸንፌአለሁ  ማለታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃዋሞ ተቀሰቀሰ። ባለስልጣናትም በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞችን አሰሩ። በብዙዎች ላይ የተለያዩ ቅጣቶችን ወይንም ከአንድ ሳምንት እስከ ሁለት ሳምንታት የሚደርሱ አስተዳደራዊ እስሮችን አስተላለፉ፤ በአንዳንዶች ላይ ደግሞ መረር ያለ ክስ መሰረቱ። እስከ ህዳር 22 ድረስ ቢያንስ አስር የሚሆኑ ጋዜጠኞች በቤላሩስ ለእስር ተዳርገዋል። እነዚህም እስረኞች ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በዚያች ሀገር ውስጥ ሲ.ፒ.ጄ ባደረገው ቆጠራ ዝርዝር ውስጥ የሚገኙ ናቸው

በፖለቲካ አለመረጋጋት ተጀምሮ ወደ ትጥቅ ግጭት ባመራው የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ባለስልጣናት በጋዜጠኞች ላይ ወከባ እንዲፈጽሙና ለእስርም እንዲዳርጓቸው ምክንያት ሆኗል። ባለፈው አመት በሀገሪቱ ታስሮ የነበረው ጋዜጠኛ አንድ ብቻ የነበር ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ቢያንስ ሰባት የሚሆኑ ጋዜጠኞች ታስረዋል። ብዙዎቹ የታሰሩት ጸረ-መንግስት ወንጀል ፈጽማችኋል ተብለው ቢሆንም፣ ባለስልጣናቱ ምርምር እናደርጋለን በሚል ሰበብ ያለምንም መረጃ የተከሳሾችን የእስራት ጊዜ እያራዘሙት ይገኛሉ።

የታሰረ ጋዜጠኛ ሁሉ በፀረ መንግስትነት በሚከሰስባት ቱርክ፣ ከከሸፈው የሐምሌ 2008 ዓ.ም መፈንቅለ መንግስት ወዲህ የሚታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ፣ መፈንቅለ መንግስቱን ተከትሎ፣ የታሳሪዎቹ ቁጥር እጅግ አሻቅቦ ነበር፡፡ የሚዲያ አውታሮች በመዘጋታቸው እና የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ነጋዴዎች ተቋማትን  በመውረሳቸው፣ ዋና ዋና የዜና አውታሮች በሕግ አስከባሪዎች አማካይነት ተወግደዋል ማለት ይቻላል። ቱርክ አያሌ ጋዜጠኞች ለእስር ሳይዳረጉ የተከሰሱበትን ጉዳይ ውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፈቅዳለች። ሲ.ፒ.ጄ እንዳረጋገጠው፣ ቱርክ በዚህ አመት 37 ጋዜጠኞችን አስራለች። ይህ ቁጥር በ2008 ከታየው ቁጥር በግማሽ ያነሰ ቢሆንም፣ ባለስልጣናት አሁንም ጋዜጠኞችንና ጠበቆቻቸውን ማሰራቸውን ቀጥለዋል። በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ምክንያት፣ በ2012 ዓ.ም የፍርድ ቤት ሥራ ለሶስት ወራት ተቋርጦ ነበር። በዚህም የተነሳ፣ በእስር ላይ በነበሩ ጋዜጠኞች ዘንድ የእስር ጊዜያችን ይራዘምብናል የሚል ስጋት ሲያድርባቸው፣ በነጻ እንለቀቃለን የሚሉት ደግሞ በፍርሃት ተጠመድወው እንዲቆዩ ሆነዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኘው የትግራይ ክልል የተከሰተውን ጦርነት የሸሹ ትግራዋዊ ወንዶች፣ በምስራቃዊ ሱዳን፣ ጋዳሪፍ ውስጥ በሚገኘው ኡምራ ኩባ የመጠለያ ካምፕ ተጠልለው ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም ዜና ሲከታተሉ። ግጭቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቢያንስ ሰባት ጋዜጠኞችን አስረዋል። (ኤፒ/ናሪማን ኤል-ሞፍቲ)

ሲ.ፒ.ጄ አካሂዶት ከነበረው ቆጠራ ጥቂት ሳምንታት በፊት፣ የቱርክ ባለስልጣናት አፍቃሪ ኩርድ ለሆነው ለሜስፓተሚያ የዜና ድርጅት የሚሰሩ በመንግስት ላይ የሰላ ትችት የሚንዝሩ ቢያንስ ሶስት የሚሆኑ ጋዜጠኞችን አስረዋል። ከነዚህ መሃል፣ አስረውና አሰቃይተው ከሄሊኮፕተር ላይ ወርውረዋል፤በዚህም የተነሳ አንደኛው ሞቷል፣ ብሎ የዘገበው ሰሚል አጉር የተባለው ጋዜጠኛ ይገኝበታል። (የቱርክ ባለስልጣናት በበኩላቸው፣ ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰባቸው አንታሰርም ብለው በማንገራገራቸው ነው ሲሉ ይሞግታሉ)።

“ህዳር 22 ቀን፣  ኢራን ውስጥ 15 ጋዜጠኞች ታስረዋል፡፡ ከነዚህም መካክል፣ ታህሳስ 3 ቀን፣ የኢራን ባለስልጣናት፣ ስለላ፣ የሀሰት ዜናዎችን በውጭ ሀገራት ማሰራጨትን እና የእስልምና እሴቶችንና የበላይ መሪውን ማንቋሸሽን ጨምሮ በ17 ወንጀሎች የተከሰሰውን ሮሆላህ ዛም የተባለውን ጋዜጠኛ በስቅላት ቀጥትዋል። አማድ ኒውስ የተባለው የዛም ድረ-ገፅና የቴሌግራም ቻነል፣ በኢራን ባለስልጣናት ላይ የሰላ ትችት ያዘለ ዘገባን ያቀርብ እንደነበርና የ2010 የተቃውሞ ሰልፍ ይደርግ የነበረበትን ጊዜና ቦታ ያጋራ እንደነበር ይታወሳል ። ዛም፣ በ2012 ዓ.ም፣ በባግዳድ ኢራቅ ውስጥ ታስሮ ከቆየ በኋላ የሞት ፍርድ ወደተፈረደበት ወደ ኢራን ተወስዷል።”

ከሲ.ፒ.ጄ አመታዊ ቆጠራ የተገኙ ሌሎች ግኝቶች የሚከተሉትን ይጭምራሉ፣

  • በእስር ላይ ከሚገኙ ጋዜጠኛ እስረኞች መካከል ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት የተከሰሱት እንደ  ሽብርተኝነትና በሕግ በታገዱ ቡድኖች አባልነት ባሉ ጸረ-መንግስት ወንጀሎች ነው።
  • 19% በሚሆኑ ክሶች ጋዜጠኞች በምን እንደተከሰሱ ግልጽ አልተደረገም፤ ከእነዚህ ጋዜጠኞች መካከል፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙት በኤርትራ ወይም በሳውዲ አረቢያ ነው።
  • በዓለማቀፍ ደረጃ ከታሰሩት መሀል፣ ሁሉም ጋዜጠኞች በሚባል ደረጃ፣ ስለሀገራቸው የሚዘግቡ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች ናቸው።
  • ሲ.ፒ.ጄ እንዳመላከተው፣ ቢያንስ 7 የሚሆኑት የውጭ ሀገር ወይም ጥምር ዜግነትት ያላቸው ሲሆኑ የታሰሩትም ኤርትራ፣ ዮርዳኖስ እና ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ነው።
  • ከታሰሩት መሀል፤ 36 ወይም 13% የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ከፊሎቹ በኢራን ወይም በሳውዲ አረቢያ ስላለው የሴቶች መብት ሲዘግቡ የነበሩ ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ደግሞ በቤላሩስ የተቀሰቀሰውን ተቃዋሞ በመዘገብ ላይ እንዳሉ የታሰሩ ናቸው።

የሲ.ፒ.ጄ ቆጠራ በያመቱ በታተመው መረጃ ላይ መጠነኛ ማስተካከያ ይደረግበታል። ይህም የሚሆነው፣ ቀደም ባሉ አመታት ስለተከሰቱ እስራቶች፣ ከእሰር መለቀቅ ወይም ሞትን አስመልክቶ ሲ.ፒ.ጄ ተጨማሪ መረጃ በሚያገኝበት ጊዜ ነው። በዚህ ዓመት፣ በነሃሴ ወር 2011 ዓ.ም በካሜሩን ስለተከሰተው የሳሙኤል ዋዚዚ ሞትና በ2008 ዓ.ም. ደግሞ በሶርያ ስለሞተው ጋዜጠኛ ጂሃድ ጀማል ሞት ሲ.ፒ.ጄ ሰምቷል። ይሁን እንጂ፣ ሲ.ፒ.ጄ  በ2012 ባደረገው ጥናት፣ ከርሱ እውቅና ውጭ ሶስት ጋዜጠኞች በ2011 ዓ.ም እንደታሰሩ አረጋግጧል። በዚህም መሰረት፣ በ2011 ዓ.ም የእስር ቤት ቆጠራ፣ 251 ታሳሪዎች እንዳሉ ያሳያል። መጀመሪያ የታተመው ዝርዝር ግን ታሳሪዎቹ 250 መሆናቸውን ያሳያል። ቀደም ባሉ አመታት የታተሙ የቆጠራ ዝርዝሮችም እንዲሁ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል። የጀማል መሞት፣ በ2008 ዓ.ም ተመዝግቦ የነበረውን የእስረኞች ቁጥር (በአመቱ የምንጊዜም ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ የተመዘገበውን ማለት ነው) ከ273 ወደ 272 ዝቅ እንዲል አድርጎታል። 

የጥናቱ ዘዴ

የእስር ቤቱ ቆጠራ የሚያካትተው በመንግስት እስር ቤት የታሰሩ ጋዜጠኞችን ብቻ ነው። ደብዛቸው የጠፋ ወይም መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት ታፍነው የተያዙ ጋዚጠኞችን አይጨምርም። እንደዚህ ያሉት  ”የጠፉ” ወይም “የተጠለፉ” በሚል አርዕስት ውስጥ የሚፈረጁ ናቸው።

ሲ.ፒ.ጄ የጋዜጠኝነት ባለሙያ ማለት ዜና የሚሰራ ወይንም በሕብረተሰብ ጉዳይ ላይ በየትኛውም የሚዲያ አይነት ሕትመት፣ ፎቶግራፍ፣ ራዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ድረ-ገዕን ጨምሮ አስተዯየት የሚያቀርብ ሰው በማለት ይተረጉመዋል። ሲ.ፒ.ጄ በዓመታዊ የእስር ቆጠራው ያካተታቸው በጋዜጠኝት ሥራቸው ምክንያት ብቻ ለእስር የተዳረጉትን ነው።

ሲ.ፒ.ጄ ጋዚጠኞች ሥራቸውን በመስራታቸው ሊታሰሩ አይገባም ብሎ ያምናል። ባለፈው አመት፣ ሲ.ፒ.ጄ ባደረገው የመብት ማቀንቀን መሰረት፣ በዓለማቀፍ ደረጃ ቢያንስ 75 የሚሆኑ እስረኞችን ከስር ጊዚያቸው በፊት እንዲፈቱ አድርጓል። 

የሲ.ፒ.ጄ ዝርዝር የያዘው እስከ ህዳር 2013 ዓ.ም በእስር ላይ የነበሩትን የጋዜጠኛን ቁጥር ነው። አመቱን ሙሉ ሲታሰሩና ሲፈቱ የነበሩትን የጋዜጠኞች ዝርዝር አላካተተም። እነዚህ ጉዳዮች የሚገኙት በhttp://cpj.org/ ነው። አንዴ በሲ.ፒ.ጄ ውስጥ የተካተቱ ጋዜጠኞች፣ ድርጅቱ በማያሻማ መልክ ከእስር መለቀቃቸውን ወይም በእስር ላይ እያሉ መምታቸውን ካላረጋገጠ በስተቀር በዝርዝሩ ውስጥ እንደተካተቱ ይቆያሉ።