በመስሉ ላይ አዲስ አበባ በሚገኝው በኦሮሚያ ኒውስ ኔትዎርክ ስቱዲዮ ውስጥ በቀን ግንቦት 17፥ 2013 ዜና ሲያነብ የሚታየው ጋዜጠኛ ደሱ ዱላ፥ በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከታሰሩት በርካታ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነው (ሬውተርስ/ቲክሳ ነገሪ)

የኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት በአንድ ወቅት ከፍተኛ ተስፋ ፈንጥቆበት የነበረውን የፕሬስ ነፃነት ደብዛውን አጠፋው

በሙቶኪ ሙሞ

አውሎ ሚዲያ ሴንተር የተሰኘው የኢትዮጵያ ኦንላይን የዜና አውታር የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድን አስተዳደር በመተቸቱ ከመንግስት በሚደርስበት “ጫና እና መሰናክል” የተነሳ  ድርጅቱን ዘግቶ  ሰራተኞቹን በሙሉ ለማሰናበት መገደዱን በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በፌስቡክ ገፁ ባሰፈረው ልጥፍ አስታውቋል።

የሚዲያ ሪፖርትስ እና የሲፒጄ ዘገባ እንደሚያስረዳው፣ ድርጅቱ የተዘጋው፣ በሐምሌ ወር መጀመሪያ አካባቢ በርካታ የአውሎ ሚዲያ ሴንተር ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ሰራተኞች፣ ከማንም ጋር ግንኙነት እንዳያደርጉ ባልተፈቀደበት ሁኔታ፣ በምስራቅ ኢትዮጵያ በሚገኝ አንድ የጦር ካምፕ ውስጥ ለሳምንታት ታስረው ከቆዩ በኋላ ነው። የአውሎ ሚዲያ ሴንተር እንደሚለው፣ የሰራተኞቹን ከእስር መለቀቅ ተከትሎ፣ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚገኙትን የድርጅቱን  ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ እና ተወርሰው የነበሩ ንበርቶች እንዲመለሱ የተላለፈውን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለመፈጸም የጸጥታ  አካላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የድርጅቱ እንቅስቃሴ ሽባ እንዲሆን ተደርጓል።

በአውሎ ሚዲያ ሴንተር ላይ የተፈጸመው አፈና፣ ኢትዮጵያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እየሰመጠች ባለችበት ወቅት፣ የመገናኛ ብዙኃን ምህዳር ምን ያህል እየከፋ እንደመጣ ያሳያል። በፌደራል መንግስት እና ለሶስት አስርት ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያን በበላይነት ሲያስተዳድር ከነበረው ጨቋኝ የፖለቲካ ቡድን፣  በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሀት) መካከል ለአንድ አመት ያክል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎችንም አፈናቅሏል። የተወሰኑ የሀገሪቱ ክፍሎችም ለረሃብ አጋልጧል

ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ፣ ሲፒጄ የበርካታ ጋዜጠኞችን መታሰርን ጨምሮ አያሌ የፕሬስ ነፃነት ጥሰቶችን ሰንዷል። በሲፒጄ አመታዊ የታሰሩ ጋዜጠኞች ሪፖርት መሰረት፣ እስከ ሕዳር 22፣ 2014 ድረስ ዘጠኝ ጋዜጠኞች በእስር ላይ ይገኛሉ። በሕዳር ወር በተደረጉት ተከታታይ እስሮች ምክንያት ለሲፒጄ ተጨማሪ የእስር መረጃዎች የደረሱት ሲሆን፥ ማጣሪያ እያደረግን እንገኛለን።

ሌሎች በመገናኛ ብዙሃን  ዙሪያ  ሲፔጄ ካረጋገጣቸው ሁነቶች መካከል የአንድ ጋዜጠኛ መገደል (ይህም ከ1990  ወዲህ  በሲፒጄ የተሰነደ የመጀመሪያው ግድያ ሆኖ ተመዝግቧል)፣ ጦርነቱን ይዘግቡ ከነበሩ ጋዜጠኞች መካከል ቢያንስ የአንድ የውጭ ጋዜጠኛ መባረር፣  ገለልተኛ የዜና ድረ-ገጽ የሆነው አዲስ ስታንዳርድ ለአንድ ሳምንት መታገድ፣ በፕሬስ አባላት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እና ማስፈራራቶች፣ እና በአብዛኛው የሰሜን ኢትዮጵያ  ክፍል የኢንተርኔት መቆራረጥ ይገኙበታል።

 በህዳር ወር ሲፒጄ ካነጋገራቸው አስር ጋዜጠኞች መካካል አንደኛው፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሚዲያ ተስፋ ቆርጫለሁ። ይህ አነጋገር ጨለምተኛ እንደሆነ ባውቅም የሚስማኝ ስሜት ግን ይኸው ነው” ብሏል። እንደ ሌሎች ቃለ መጠይቅ እንየተደረገላቸው ሁሉ፣ ይህ ጋዜጠኛም፣ ለአንድ አለም አቀፍ ድርጅት አስተያየት በመስጠቱ ሊወስድበት የሚችለውን እርምጃ በመፍራት ማንነቱ እንዳይገለጽ ጠይቋል።

ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለእስር የተዳረጉት አብዛኛዎቹ ጋዜጠኞች ትህነግን ትደግፋላችሁ በሚል እና ክስ ለመመስረት የማያስችል ግልጽ ያልሆነ ውንጀላ እንደቀረበባቸው የሲፒጄ ጥናት ያሳያል። ከእነዚህ ጋዜጠኞች መካከል፣ ብዙዎቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ፖሊስ፣ መቋጫ በሌለው የፍርድ ሂደት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል በሚል ሰበብ የተወሰኑ ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር የማቆየቱን ዘዬ ስራዬ ብሎ ይዞታል፤ ይኸው የሲፒጄ ጥናት እንደሚያሳየው፣ ጋዜጠኞች በዋስ እንዲፈቱ  በፍርድ ቤት የሚተላለፈውን ትዕዛዝ ፖሊስ ተፈጻሚ እንዳይሆን ችላ ብሏል ወይም አዘግይቷል። ለምሳሌ፣ክብሮም ወርቁ የተባለ የሬድዮ ጋዜጠኛ  እና ተቀማጭነቱን  ኬንያ ውስጥ ላደረገ ብሔራዊ ሚዲያ ቡድን የሚዘግበው ጋዜጠኛ ተስፋ አለም ተክሌ፣ በህዳር ወር መጨረሻ ላይ የዋስ መብታቸው ተጠብቆ ከስር እንዲፈቱ በፍርድ ቤት ቢወሰንም፣ በእስር እንዲቆዩ ተደርጓል።

 “አሁን እየጠየቅሁ ያለሁት እንዳልታሰር አይደለም። እየጠየቅሁ ያለሁት፣ ራሴን እንድከላከል በሚፈቅድልኝ እና አንዴ ካምፕ ውስጥ ከወረወረኝ በኋላ በማይረሳኝ መንግስት እንድታሰር ነው” በማለት  አንድ ሌላ ጋዜጠኛ ከሲፒጄ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።

ጥቅምት 23 ቀን፣ የፌደራል መንግስቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓል፤ ይህ ገደብ-የለሽ ህግ፣ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረጉ ፍተሻዎችን፤ ምናልባትም የጊዜ ገደብ የሌለው እስራትን፤ እና የፍርድ  ሂደቶችን  እንዳይካሄዱ ይፈቅዳል። ሕጉ፣ “ለአሸባሪ ድርጅቶች በቀጥተኛ ወይንም በተዘዋዋሪ መልክ የሞራል ወይም የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የተጠረጠሩ” የሚዲያ ተቋማትን የስራ ፈቃድ በጊዚያዊነት ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲያግዱ ለተቆጣጣሪ አካላት ሥልጣን ሰጥቷል።

“በተዘዋዋሪ መልክ የሚደረግ የሞራል ድጋፍ ምን ሊያካትት እንደሚችል ማንም አያውቅም። ጸሎት ነው ወይስ ምኞት? ወይስ አንድ መጣጥፍ?›› በማለት አንድ የጋዜጣ አዘጋጅ በመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ላይ ግርምቱን አስፍሯል። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኋላ፣ ስለጦርነቱ የሚያወግዙ ዘገባዎችን አላማቀርብ መጀመራቸውንም አዘጋጁ ተናግሯል።

የሀገሪቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ፣ አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ፣ ታስረው እንደነበር የሚገልጽ ግምቱን አስቅምጧል። ሲፒጄ እንደሰነደው፣ የዐብይ መንግስት ከመምጣቱ በፊት ተደንግጎ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ ጋዜጠኞች እና መገናኛ ብዙሃን የእስር እና የአሰራር ገደብ ኢላማ ሆነው ነበር። በ2010 አጋማሽ ላይ የዐቢይን ጠቅላይ ሚንስትር መሆን ተከትሎ የመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ለዓመታት ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች ነጻ እንዲወጡ አድርጓል፤ ይህም በአንድ ወቅት በዓለም ላይ ከፍተኛ የሳንሱር ቁጥጥር ከሚደረግባቸው ሃገራት አንዷ በነበረችው ኢትዮጵያ አዲስ የሚዲያ ተስፋን እንዲፈነጥቅ አስችሏል።

አሁን፣ ኢትዮጵያ እንደገና ከሰሃራ በታች ከሚገኙ የአፍሪካ  ዋነኛ አስከፊ የጋዜጠኞች አሳሪ ሀገሮች መካከል  አንዷ ሆናለች።

ባለስልጣናት ሕዳር 16 ካወጡት መግለጫ መረዳት እንደሚቻለው፣ ኦፊሴላዊ ያልሆኑ “ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን የተመለከት መረጃን ማሰራጨትና በማንኛውም ሚዲያ የጦር ግንባር ውሎ ዜናዎችን እና ውጤቶችን መዘገብ” የሚከለክሉ ጥብቅ የህግ ገድቦችን አስቅምጠዋል፤ “የመረጃ ነፃነትን ሽፋን አድርጎ መንቀሳቀስንና አሸባሪ ቡድኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋሪ መልክ መደገፍ” እንደማይቻልም ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። የቀጠናው የፕሬስ መብት አካል የሆነው “የውጭ ፕሬስ ማህበር አፍሪካ” (Foreign Press Association Africa) ሊቀመንበር ኬኔዲ ዋንዴራ በኢሜይል በላኩት መግለጫ፣ በቅርቡ የወጣው ትዕዛዝ “በሀገሪቱ ውስጥ ላሉ ሚዲያዎች እየመጣ ስላለው ሁኔታ መጥፎ ምልክት ነው” በማለት ለሲፒጄ ገልጸዋል ።

ተቀማጭነቱን ካናዳ ያደረገውና በግሉ የሚሰራው ጋዜጠኛ ዘካርያስ ዘላለም፣ በመልዕክት መላላኪያ አማካኝነት ለሲፒጄ እንደ ተናገረው፣ “በሀገሪቱ ያሉ ጋዜጠኞች በጦርነቱ ወቅት እንዴት መዘገብ፣ መጻፍ እና የአርታኦት ስራ መስራት እንዳለባቸው ማስተካካያ እንዲያደርጉ ተገደዋል። ይህም [ኦፊሴላዊ ያልሆነ መረጃ ማስተላልፍ ላይ የተደርገ እቀባ] ለአመታት በመገናኛ ብዙኃን ላይ ሲደርስ የነበረውን እና ቀድሞውኑም ተንኮታኩቶ ያለውን የሚዲያ ጥቃት የሚያስቀጠል ነው።”

ህዳር 21 ቀን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሳቢያ የመገናኛ ብዙሃን “እንዲጨፈለቁ ተድርገዋል” የሚሉ ዘገባዎች “ሆን ተብለው የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች ናቸው” ብለዋል። የጋዜጠኞችን መታሰር፣ የአውሎ ሚዲያ ማዕከል መዘጋትን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ማብራሪያ እንዲስጠው ሲፒጄ ሕዳር 21 ቀን ለላካቸው ኢሜይሎች ከቢልለኔም ሆነ ከፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ሀሴቦን ምላሽ አላገኘም። የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባዩ ጄይላን አብዲ ሲፒጄ በሕዳር 29 ላቀረበላቸው ተመሳሳይ የስልክ ጥያቄ “በጋዜጠኝነቱ ምክንያት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ የታሰረ ሰው የለም” ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል። ነገር ግን ጄላን በተለዮ ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ጠቅሰው መረጃ አልሰጡም።

የአውሎ የዜና ተቋም መዘጋት እንደሚያሳየው፣ ይህ በፕሬስ ላይ የሚደርሰው ጥቃት የሚሰቀጥጥ ተጽእኖ አሳድሯል። ባለፈው አንድ አመት የታሰሩ አራት ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ሙያውን እንዳቋረጡ ወይም እራሳቸውን ደብቀው ስለነበር ስራቸውን መስራት እንዳልቻሉ ለሲፒጄ ተናግረዋል።

አንድ ጋዜጠኛ፣ “ከእስር ብፈታም፣ ነጻ አይደለሁም” ሲል አማሯል።

ሙቶኪ ሙሞ የሲፒጄ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ተወካይ ናት። መቀመጫዋን በኬንያ ናይሮቢ ያደረገች ሲሆን፣ ከሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት እና ግሎባላይዜሽን የማስተርስ ዲግሪ አግኝታለች።