በዋሽንግተን ዲ.ሲ. በጃንዋሪ 6፣ 2021 በአሜሪካ ካፒቶል ሒል ከተካሔደው አመፅ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የፌደራል ምርመራዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ጋዜጠኞች ለሲ.ፒ.ጄ. እንደገለፁጽ በአንድ በኩል አመፁ የተቀጣጠለው በአሁኑ ወቅት ዓለማቀፍ በሆነው ምርጫን አስመልክቶ አየተካሄደ ባለው የሀሰት ትርክት ነው (ጌቲ ኢሜጅ/ኤኤፍፒ/ብሬንት ስታይርቶን)

ምርጫን የተመለከተ የተሳሳተ መረጃ በዓለም ዙሪያ እየተከሰተ ነው፤ እነዚህ ጋዜጠኞች ደግሞ እየተፋለሙት ነው

በሪቤካ ሬድሌሞር/የሲ.ፒ.ጄ ኦዲየንስ ኢንጌጅመንት አስተባባሪ

ታህሳስ 28 ቀን 2013 ላይ በተደረገው የካፒቶል የዓመጽ ሰልፍ ዙሪያ ምርመራ እየተካሄደ ባለበት ሁኔታም፣ አሁን ድረስ ስለ አሜሪካ ምርጫ የሚሰራጨው ሀሰተኛ መረጃ አሳሳቢነት እንደቀጠለ ነው፡፡ ይህን አይነት ክስተት እየተጋፈጠች ያለቸው ግን አሜሪካ ብቻ አይደለችም፡፡ በተለይ እንደ ብሄራዊ ምርጫ ካሉ ታላላቅ ሁነቶች ጋር በተያያዘ የሀሰትኛ መረጃ ስርጭት በዓለም ዙሪያ እየተከሰተ ነው፡፡

የበዝፊድ ኒውስ (BuzzFeed News ) ዘጋቢው ጄን ሊቲቪንኔንኮ ስለተሳሳተ መረጃው ውዝግብ ለሲፒጄ በስልክ ሲገልጹ፣ “ይህ ቋንቋ ምትሃታዊ ነው፤ እሱ ክልላዊ ምትሃት ነው፤ ድንበሮችን አያከብርም” ሲሉ ተናግረዋል፤ አክለውም፣“ለማሟረት አይደለም፣ ግን ይህ ሁኔታ በምርጫዎችም ሆነ ከምርጫዎች ውጭ የሚቀጥል መሆኑን የሚያሳዩ አዝማሚያዎችን እያያን ነው” ብለዋል።

የሀሰት መረጃ ከልክ በላይ ሲባዛ፣ ጋዜጠኞች መረጃውን ለማስተካከል በመሞከር ቁልፍ ድርሻ ይኖራቸዋል። የተሳሳተ መረጃን ለመከላከል በተቋቋመው “ፈርስት ድራፍት” (First Draft) በተባለ የአሜሪካ የምርምር ማዕከል በምክትል ዳይሬክተርነት የሚያገለግሉት አይሜ ሪንሃርት፣ “ጋዜጠኞች የትኛው የፖፕ ዝንብ እንደሚፈለፈል ለማወቅ ያሰፈሰፉ እና ለመያዝም የሚጠባበቁ ይመስሉኛል” በማለት ለሲፒጄ በስልክ ተናግረዋል። 

ውጤቱ በተቃዋሚዎች ዘንድ ተቀባይነት ባያገኝም፣ የተሳሳተ መረጃ ስርጭትን እንደ አንዱ የምርጫ መመሪያቸው አካል አድርገው የተወዳደሩት የሰርቢያና የቬኒዚዌላ ገዥ ፓርቲዎች፣ የስልጣን መንበራችንን ለማደላደል ያስችለናል ብለው ያካሄዱትን ምርጫ አሸንፈዋል፤ የሀሰትኛ መረጃ ስርጭት፣ በግንቦት ወር በኢትዮጵያ በሚካሄደው ምርጫም ተመሳሳይ ሚና ሊኖረው እንድሚችል ይገመታል።  የተሳሳተ መረጃ ስርጭትን አስመልክቶ፣ የእነዚህን ሀገራት ጋዜጠኞች ሲፒጄ አነጋግሯል። የስርጭቱ መጠን ይብዛም ይነስም፣ የተሳሳተ መረጃ ስርጭትን መዘገብ አስፈላጊ መሆኑን አና ስርጭቱንም እንዴት ማስተካከል እንድሚችሉ ጋዜጠኞቹ ለሲፒጄ ተናግረዋል። 

ሰርቢያ

ሰርቢያ፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሚያዝያ 2012 ላይ አስተላልፋው የነበረውን ፓርላሜንታዊ ምርጫ፣ ሐምሌ 14 ቀን አካሂዳለች። የሰርቢያው ፕሬዝዳንት አሌክሳርዳር ቩሲስ የሚመሩት የሰርቢያ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ በሀገሪቱ ፓርላማ ውስጥ አብዛኛዎቹን መቀመጫዎች አሸንፏል፡፡ ይህን ተከትሎም፣ የተቃዋሚው ፓርቲ ምርጫው ተጭበርብሯል በማለት የምርጫውን ውጤት አልተቀበለውም። ምርጫው የተካሄደው፣ የሰርቢያ የዴሞክራሲ መመዘኛ ጉድለት በታየበት፣የመገናኛ ብዙሃን በመንግስት ቁጥጥር ስር በሆነበት እና መራጮች በወረርሽኙ ፍራቻ በተወጠሩበት ሁኔታ ስለነበረ፣ የምርጫው ፍትሃዊነት  አጠያያቂ ነው ሲሉ ተቃዋሚዎቹ ያማርራሉ፡፡

ምርጫው ከመድረሱ አስቀድሞ በሰርቢያ የእውነት አጣሪ ድርጅት፣ ኢስቲኖመር (Istinomer) ወይም በእንግሊዘኛው ትሩዞሜትር( Truth-o-Meter)፣ፕሬዘዳንቱን ከፍ ከፍ ለማድረግ፣ በፕሬዚዳንቱ እና በደጋፊዎቻቸው ይሰራጩ የነበሩትን የተሳሳቱ የምረጡኝ መረጃዎች ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ለምሳሌ፣ ድምፅ ከመስጠት ሂደቱ ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ፣ ቩሲስ ለአረጋውያን ዜጎቻቸው በላኩት የምረጡኝ ዘመቻ ደብዳቤ፣ ሰርቢያ በአውሮፓ ውስጥ በጣም ዝቅተኛ የሆነ ኮቪድ-19 የሞት ቁጥር ካስመዘገቡ ጥቂት ሃገራት አንዷ ነች ብለው እንደነበር የኢስቲኖመር ቡድን አረጋግጧል ሲሉ፣ የኢስቲኖመር ጋዜጠኛ ሚልጃና ሮጋ ለሲፒጄ በስልክ ተናግረዋል፡፡ ይሁንና፣ ኢስቲኖመር፣ እውነታን ለማጣራት ባደረገው ዳሰሳ፣ በወቅቱ ቢያንስ 20 የሚሆኑ የአውሮፓ ሀገራት፣ ዝቅተኛ የሞት መጠን አስመዝግበው እንደነበር ዘግቧል፡፡

ሮጋ ለሲፒጄ እንደተናገሩት፣ በዘመቻው ወቅት፣ “ኮሮና ቫይረስን አሸንፈነዋል፤ እኛ ያን ያህል ጥሩዎች ነን፤ አሸንፈናል” የሚሉ መልዕክቶችን እንሰማ ነበር። ከምርጫው በኋላ ግን፣ የኮቪድ ተጠቂዎች ቁጥር እጅግ በሚስደነግጥ ሁኔታ አሻቅቧል። 

ከምርጫው በኋላ ባሉት ቀናት፣ “ምርጫው እጅግ የሰከነ፣ እንከን የለሽ እና የምርጫ ዘመቻውም አቻ የማይገኝለት ነበር” ሲሉ ቩሲስ ያሰሙትን ዲስኩር ኢስቲንሞር አጣጥሎታል። የእውነት-አጣሪው ቡድን፣ገለልተኛ የሆኑ የምርጫ ታዛቢዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው፣ በምርጫው ወቅት ሙስና፣ ስርዓተ-አልበኝነትና ያልተገቡ የህጎች ለውጥ ታይተው ነበር ይላል። ሮጋ ለሲፒጄ እንደነገሩት፣ “ስለ ምርጫው ሂደት የነበረውን ዘገባ በመመርኮዝ ይህ ሁሉ [ቩሲስ ያሰሙት ዲስኩር] ትክክል አልነበረም ማለት ይቻላል። ”

ሮጋ እና ባልደረቦቻቸው እውነታን የማጣራት ሥራቸው ሲያከናውኑ መዋከብ ደርሶባቸዋል፡፡ የገዢው ፓርቲ አባላት፣ ታብሎይዶች (tabloids) እና  ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች፣ “ጠላት” ብለው እንደሚጠሩዋቸው እና የተቃዋሚ ፓርቲ አፈቀላጤ አድርገው እንደሚቆጥሯቸው” ሮጋ ይናገራሉ። ጥቃቶቹ አንዳንዴም ከዚህ የከፉ ነበሩ፡፡ “ከአንድ ዓመት በፊት፣ ማለትም ልክ የድረገጻችንን 10ኛ ዓመት ካከበርን በኋላ፣ የበይነመረብ [DDoS] ጥቃት ዒላማ ሆነን ነበር” ይላሉ ሮጋ፣ “ሁኔታው የሚረብሽ ነበር፡፡ በድንገት ሁሉም ነገር ተንኮታኮተ፡፡ በእውነቱ በጣም አሰቃቂ ነበር። ”ጥቃቱን ተከትሎ፣ቡድኑ ለሰርቢያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አቤቱታ አሰምቶ ነበር፤ ቡድኑ ስሞታውን ካሰማ አንድ ዓመት ቢያልፈውም እስካሁን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ምንም አይነት ምላሽ እንዳላገኘ ሮጋ ይናገራሉ ፡፡

“እንደ ጋዜጠኞች፣  ማድረግ የምንችለው ተስፋ አለመቁረጥ ብቻ ነው፤” ሲሉ ሮጋ ለሲፒጄ ተናግረዋል፤ ጥያቄዎችን በመጠየቅ፣ ለተቋማት፣ ለፖለቲከኞች እና ለመንግስት ባለሥልጣናት በመደወል መኖራችንን እያሳያን ነው፡፡ እውነትን ለማግኘት ወደ ኋላ አንልም፡፡”

አንድ የሰርቢያ መንግስት ቃለ አቀባይ ሰለ ጉዳዩ ለሲፒጄ አስተያየት እንዲሰጥ በኢሜል ተጥይቆ ምላሽ አልሰጠም:: 

በግራ በኩል፤ የሰርቢያ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ቩቺ (መሃል) ሰኔ 14 ቀን 2012 በሰርቢያ፣ ቤልግሬድ ውስጥ በሚገኘው የምርጫ ጣቢያ ድምፃቸውን ለመስጠት ወረፋ በመጠበቅ ላይ እንዳሉ(AFP / Andrej Isakovic)። በቀኝ በኩል፤: ህዳር 27 ቀን 2013 በካራካስ፣ ቬኔዙዌላ ውስጥ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ መራጮች በአንድ የምርጫ ጣቢያ ተሰልፈው(AFP/Yuri Cortez)። ሁለቱም ምርጫዎች በተቃዋሚዎች  ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም፡፡

ቬኒዙዌላ

በሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቀባይነት ባላገኘው የህዳር 27፣ 2013 ዓ.ም. የፓርላማ ምርጫ፣ የቬኒዙዌላ ፕሬዝዳንት

ኒኮላስ ማዱሮ አጋሮች አብዛኛዎቹን የምክር ቤት መቀመጫዎች አሸንፈዋል። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ በተቃዋሚዎች ተይዞ የነበረውን የቀድሞ ምክር ቤት ሳያማክር የምርጫ ኮሚሽኑን በመሰየሙ፣ አስቀድሞም ቢሆን የምርጫው ሂደት ወደ ማዱሮ እንዲያጋድል ድጋፍ ሰጥቷል በማለት በፍርድ ቤቱ ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። 

በዚህ ተቃውሞ መሀል፣ በማዱሮ ጥምር መንግስት የተካተቱ የፖለቲካ መሪዎች፣ መንግስትን የሚደግፉ የዜና አውታሮች እና በመንግስት ባለቤትነት በሚተዳደሩ ተቋማት የሚሰሩ ጋዜጠኞች፣ የህግ አውጭውን የምርጫ ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ ያግዛሉ ያሏቸውን መልዕክቶች በኢንተርኔት ሲያዥጎደጉዱ እንደከረሙ፣ የቬኒዞላውያን የፕሬስ ነፃነት ድርጅት (አይፒዋይኤስ) ዳይሬክተር፣ ማሪያኔላ ባልቢ፣ ለሲፒጄ  በስልክ ነገረውታል።

“የመንግስት ዓላማ የድል ብስራትን፣ የምርጫውን ሕጋዊነትንና፣ ምርጫው ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ እንደነበረው የሚያሳዩ  ትርክቶችን [በህዝብ ላይ] በግድ መጫን ነው”፣ ይላሉ ባልቢ። 

ለምሳሌ፣ የብሔራዊ የምርጫ ምክርቤቱ (ሲኤንኢ) በትዊተር አካውንቱ ላይ፣ ከአሜሪካ የመጡትን ታዛቢዎችጨምሮ፣ የዓለም አቀፍ ታዛቢዎች በምርጫው ላይ ቁጥጥር አድርገዋል የሚል ማረጋጋጫ አስፍሯል–ይሁን እንጂ፣ ይህንን አባባል “የአሜሪካ ልዑክ ለአሜሪካ ግዛቶች ድርጅት”( the U.S. Mission to the Organization of American States) ፉርሽ ያደርገዋል። 

ባልቢ ለሲፒጄ እንደአብራሩት፣ ስምንት አባላት ያሉት የእርሳቸው ቡድን፣ በምርጫው ሂደትና በምርጫው ዕለት ይናፈሱ የነበሩ የሀሰት መረጃዋችን ቢያውቅም፣ የመረጃውን ፍሬቢስነት ሳያጋልጥ መቆየትን መርጧል፤ ቡድኑ ይህንን ማድረግ የመረጠው፣ የተጀመረው የውሸት ፍሰት ውሉን ሊስት ይችላል በሚል ጥርጣሬና ወቅቱ ሲደርስ እውነታውን ለማጋለጥ በመፈለግ ነው። ምርጫው ከተጠናቀቀ ከአንድ ሳምንት በኋላ ግን፣ ቡድኑ በስድስት ተከትታይ ጊዚያት የቀረበ እና የሀሰት መረጃው እንዴትና በማን ይሰራጭ እንደነበረ የሚያሳይ ግዙፍ የድህረ-ምርጫ ሪፖርት መድብል አሳትሟል። 

በተከታታይ ባወጣው በዚህ ሪፖርቱ፣ አይ.ፒ.አይ.ኤስ፣ የሚከተሉትን አራት. የሀሰት የመረጃ ምንጮች ለይቷል፤ አፍቃሪ-መንግስት የሆኑ የዜና አውታሮች፤ መንግሥትን የሚደግፉ ጋዜጠኞች፤እንደ ፓርቲና የምርጫ ኮሚሽን ያሉ የፖለቲካተቋማት እና የፖለቲካ መሪዎችና የመንግሥት ቃል አቀባዮች። የሀስት መረጃን የማስራጨቱ ስራ፣ በማዱሮ፣በመንግስት ደጋፊ ጋዜጠኞች እና በሌሎች ፖለቲከኞች ተጀምሮ፣ በፖለቲካ ተቋማት እና በሌሎች የመገናኛ አውታሮች መሰራጨቱን እንደቀጠለ ሪፖርቱ አመላክቷል።  

ፕሮጀክቱን ለማዘጋጀት ስላነሳሳቸው ምክንያትም ለሲ.ፒ.ጄ. ሲያብራሩ፣ ባልቢ የሚከተለውን ብለዋል፣ “ስለተፈፀመውነገር ምስክርነት–ግልጽ ምስክርነት መስጠት አለብን። ስርአት ያለውና በደንብ ተቀነባብሮ የቀረበ፣ በውል የተዘጋጀ፣ እንደ ሞዴል የሚያገልግል፣ [ለቬኒዙዌላውያን አይንና ጆሮ የሚሆን] እና የቬንዙዌላን የሚዲያ ስነምህዳር ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ምስክርነት ትተን ማለፍ ስላለብን ነው።” ይህንንም የምናደርገው፣ በዋናው ፕሪስ ያለጥያቄ ተቀባይነትን የሚያገኝ ትርክት በማበርክት ነው ብለዋል። 

የቬንዙዌላ የኮሚኒኬሽንና የመረጃ ሚኒስቴር እና የሀገሪቱ የቴሌኮሚኒኬሽን ቁጥጥር ኤጀንሲ ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ በስልክና በኢሜል ተጠይቀው ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።

ኢትዮያ 

ኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ባላፈው ነሀሴ፣ 2012 ዓ.ም አስተላልፋው የነበረውን የተውካዮች ምክር ቤት፣ የክልላዊ እና ከተማ አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ግንቦት 28፣ 2013 ዓ.ም ቀጠሮ ይዛለች። እንደ ዜና ዘገባዎች ከሆነ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የብልጽግና ፓርቲ፣ በፌደራልና በክልል ደረጃ የተሻለ ስልጣን ለማግኘት ከሚፈልጉ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በመወዳደር ስልጣኑን አስረግጦ ለመቀጠል አስቧል። የትግራይ ክልልን ለመቆጣጠር፣ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት እና በትግራይ የቀድሞ የክልሉ የመንግስት ታማኝ ኃይሎች መካከል የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ፣ በቅርቡ የታየውን የሀሰት ወሬ መስፋፋት በመጥቅስ፣ ምርጫውን አስመልክቶ ብዙ የሀሰት መረጃዎች ሊነዙ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ለሲፒጄ ተናግረዋል።

ግጭቱ እየተባባሰ ሲመጣ፣ (የተባበሩት መንግስታት የጦር ወንጀሎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያ እስከ መስጠት አድርሶታል) ሁለቱንም ሀይሎች የሚደግፉ ወገኖች በየፊናቸው የተሳሳተ መረጃን አሰራጭተዋል። ለዚህ እንደ ምሳሌ የሚሆነው፣ ቀደም ሲል ዐብይ ለተወካዮች ምክር ቤት በህዳር ወር በትግራይ ውስጥ በተካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ አንድም ሰላማዊ ሰው አልተገደለም ብለው ያቀረቡትን ሪፖርት የሚጻረር ዘገባ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ ያካባቢውን ሃኪሞች ዋቢ አድርጎ ማውጣቱ ነው። በሌላ በኩል፣ የቀድሞው የክልሉ መንግስት ደጋፊ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች፣ ተገድለዋል ያሏቸውን የፌደራል መንግስት ወታደሮች ምስል በየአካውንታቸው አጋርተዋል፤ ይሁን እንጂ፣ ምስሎቹ ከአንድ ፊልም የተወሰዱ መሆናቸውን ኤኤፍፒ አረጋግጧል። የተለያዩ የዜና ዘገባዎች እንደሚያሳዩት፣ እንደዚህ አይነት በርካታ ሌሎች ምሳሌዎች ሞልተዋል።

ስለመጪው ሁኔታ ሲያስብ፣ የሀሰት ወሬና የምርጫው ነገር እንደሚያሳስበው አንድ ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ለሲፒጄ ተናግሯል። ለደህንነቱ ሲል ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው ይህ ጋዜጠኛ፣ “ምርጫው በጣም ፈታኝ ይሆንብናል” ይላል። “ብዙ የሀሰት መረጃዎች ሲነዙ እናያለን–ጅማሬውንም እያየን ነው ያለነው።” የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበሯ ስራቻውን ለቀው ወደ አሜርካ ኮብልለዋል፤ የተፎካካሪ ፓሪቲ መሪዎች የዐብይን የብልጽግና ፓርቲ ለመቀላቅል አቅድዋል የሚሉ ከምርጫው ጋር የተያያዙ ሀሳተኛ ወሬዎች በማበህራዊ ተጠቃሚዎች አማካኝነት ሲስራጩ እንዳየ ጋዜጠኛው ጨምሮ ያስረዳል። እንደዚህ አይነት አሉባልታዎች፣ የምርጫው ጊዜ ሲደርስ፣ የመጠራጠርንና ግራ የመጋባትን ስሜት ይፈጥራሉ የሚል ስጋት እንዳለውም ጋዜጠኛው አክሎ ይናገራል።

ከምርጫው አስቀድሞ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመውና የመብቶች እና ዲሞክራሲ እድገት ማዕከል የተሰኘ ኢትዮጲያዊ ድርጅት፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን አዘጋጋብ አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ዝርዝር ስልጠናን እየሰጠ ነው። 

 “የሀሰት መረጃን እንዴት መለየት እንደሚቻል፣ እውነታውን ማጣራት እንዴት እንደሚቻል፣ ቴክኖሎጂን እና ሀብትን በመጠቀም ምርመራ እንዴት ማድረግና እውነታን ማጣራት እንደሚቻል [ስልጠና] እንሰጣቸዋለን” በማለት ታዋቂውየኢትዮጵያ ብሎገር፣ የድርጅቱ ተባባሪ መስራች እና ስራ አስፈፃሚ፣ አቶ በፍቃዱ ኃይሉ፣ለሲፒጄ በስልክ ተናግረዋል።እርሳቻው እንደሚሉት፣ እውነታን አጣርተው የሚሰሩ ስራዋች እስከአሁን ድረስ የሚታተሙት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ነው፤ በመሆኑም፣ እነዚሀ ስራዎች ለኢትዮጵያ ታዳሚዎች በስፋት ተደራሽ አልነበሩም። ስለሆነም፣ የሀገር ውስጥ ጋዜጠኞች በራሳቸው ቋንቋዎች እውነታን ማጣራት እንዲችሉ ማብቃት አስፈላጊ መሆኑን ሀላፊው አስገንዝበዋል። 

ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀው ጋዜጠኛ፣ የፌደራል መንግስቱ ደጋፊዎችም ሆኑ ተቃዋሚዎቻቸው፣ ጋዜጠኞችን ኢላማ ያደረገው የበይነመረብ ጥቃታቸው እንደቀጠለ በመሆኑ፣ በምርጫ ወቅት የፕሬስ ነፃነት ላይኖር ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው ይናገራል።  “ከዚህ በፊት ጋዜጠኞች መንግስትን ነበር የሚፈሩት–የሚፈሩት ነገር እስር ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን [የሚፈሩት] እነዚህን የማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች ወይም ግሪሳዎችን ነው፤ ምክንያቱም፣ አድራሻየላቸውማ” ብሏል።  “ስለዚህ፣ ምን መሰለህ፣ ጋዜጠኞች ይፈራሉ፤ ምክንያቱም፣ በፌስቡክ ላይ የተጻፈን ጽሁፍመሰረት አድርጎ አንድ ሰው አንዳች ጥቃት ሊያደርስባቸው ይችላል” በማለት ያክላል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ እና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ባለስልጣን ሰለ ጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡበኢሜል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም ።