Police officers detain a photojournalist during an opposition rally to protest the official presidential election results in Minsk, Belarus, Saturday, Sept. 26, 2020. Hundreds of thousands of Belarusians have been protesting daily since the Aug. 9 presidential election. (AP Photo/TUT.by)

ዓለማችን በወረርሺኝ እና ባለመረጋጋት እየተናጠች ባለችበት ባሁኑ ወቅት፣ በዓለም-አቀፍ ደረጃ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር ከምንጊዜም በላይ አሻቅቧል

በእስር ቤት ውስጥ የኮቪድ-19 አደገኛነት እየታወቀ በዓለማቀፍ ደረጃ ቢያንስ 274 ጋዜጠኞች ታስረዋል

ኒዮርክ፣ ታህሳስ 6፣ 2013–የጋዜጠኞች ተሟጋች ኮሚቴ (ሲ.ፒ.ጄ) በቅርቡ ያካሄደው አመታዊ ቆጠራ እንደሚያሳየው በ2012/13 ዓ.ም ካሁን በፊት ታይቶ በማይታወቅ መጠን፣ በርካታ ጋዜጠኞች ስራቸውን በመስራታቸው ብቻ ለእስር ተዳርገዋል። ይህም የሆነው፣ ጋዜጠኞች ስለ ኮሮና ቫይርስ ወረርሺኝ እና ስለህዝባዊ ተቃዋሞ በሚዘግቡበት ወቅት አላሰራ ብለው በሚያውኳቸው መንግስታት ነው።

“ዓለማችን በዓለማቀፍ ወረርሺኝ እየተናጠች ባለችበት ወቅት እስከ አሁን ታይቶ በማይታወቅ መጠን በርካታ ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት ሲታጎሩ ማየት በጣም የሚያስደነግጥ እና የሚሰቀጥጥ ነው” ይላሉ የሲ..ፒ..ጄ.ው ስራ አስፈጻሚ ጆኤል ሲሞን ። አክለው እንደሚሉትም፣ “እያየነው ያለነው ይህ የአፈና ማዕበል፣ የመረጃን ፍሰት የሚያደናቅፍና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭትን የሚያባብስ ተግባር ነው። ኮቪድ 19 እስር ቤቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያመሰ ባለበት ሁኔታ ጋዜጠኞችን ማሰር ህይወታቸውን አደጋ ላይ መጣል ነው።”

እስከ ህዳር 22፣ 2013 ዓ.ም ድረስ፣ ቢያንስ 274 የሚሆኑ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገዋል። ይህ አሀዝ ሲ.ፒ.ጄ መረጃ መሰብሰብ ከጀመረ ከ1980ዎቹ ወዲህ በከፍተኛ መጠን የተመዘገበ ቁጥር ከመሆኑም በላይ፣ ላለፉት አምስት ተከታታይ አመታት ቢያንስ 250 ጋዜጠኞች እየታሰሩ እንዳሉ ልብ ይሏል። ቻይና፣ ግብጽ እና ሳውዲ አረብያ ዋነኞቹ አስከፊ አሳሪዎች ናቸው።

ለብዙዎች መታሰር እንደ ምክንያት የቀረቡት ደግሞ ህዝባዊ ተቃውሞዎች እና ፖለቲካዊ ውጥረቶች ነበሩ። የታሳሪ ጋዜጠኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እያሻቀበ የመጣባቸው ሁለት ሀገራት ኢትዮጲያ እና ቤላሩስ ናቸው። በኢትዮጵያ የታሳሪዎች ቁጥር የጨመረው፣ አለመረጋጋቱ ወደ ትጥቅ ግጭት በማምራቱ ሲሆን፣ በቤላሩስ ደግሞ እንደተጭበረበረ በሰፊው የሚነገርለትን ምርጫ፣ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሽንኮቨ አሸንፌአለሁ ማለታቸውን ተከትሎ የተነሳውን ተቃዋሞ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች በመታሰራቸው ነው።

ምንም እንኳን ሲ.ፒ.ጄ ቆጠራውን ባካሄደበት ወቅት አሜሪካ ውስጥ የታሰሩ ጋዜጠኞች ባይኖሩም፣ ካሁን በፊት ባልተለመደ መልኩ የፖሊስ ጭካኔን የሚቃወሙ ሰልፎችን ሲዘግቡ የነበሩ 110 ጋዜጠኞች ታስረዋል ወይም ክስ ተመስርቶባቸዋል። የአሜሪካው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች እንደሚለው፣ ቢያንስ 12 የሚሆኑት ደግሞ ክሳቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው።

ፕሬዝደንት ትራምፕ፣ በአስተዳደር ዘመናቸው ሁሉ፣ ወሳኝ የሆኑ ዘገባዎችን ሳይቀር፣ “ሐሰተኛ ዜናዎች” ናቸው በማለት ሲያጣጥሏቸው ነው የቆዩት። ብዙ አምባገነን መሪዎችም ይህን አይነቱን አባባል በየሀገሮቻቸው ያሉ ጋዜጠኞችን ለማዋከብ እንደሽፋን ተጠቅመውበታል። በዓለማቀፍ ደረጃ፣ “የተፈበረከ ዜና” ሰርታችኋል በሚል ሰበብ የታሰሩት ጋዜጠኞች 34 ሲሆኑ፣ ያለፈው አመት ቁጥር ደግሞ 31 ነበር። ሲ.ፒ.ጄ በቅርቡ ለተመራጩ ፕሬዝደንት ባይደን የአሜሪካ የአለማቀፋዊ የፕሬስ ነጻነት የመሪነት ሚና እንደገና ስለሚያንሰራራበት ሁኔታ ምክረ-ሐሳቦችን አቅርቧል። የፕሬስ ነጻነት ጉዳዩ በውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ዘንድ ቅድሚያ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግና የፕሬስ ነጻነት ፕሬዝደንታዊ ልዩ መልክተኛን መሰየም ምክረ-ሀሳቡ ካካተተቸው መሀል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ዋና ስራ አስፈጻሚው ሲሞን እንደሚሉት፣ “በዓለም አቀፍ ደረጃ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር እስካሁን ባልታየ መጠን ማሻቀቡ፣ ፕሬዝደንት ትራምፕ ትተውልን ያለፉት ውርስ ነው። አዲሱ ተመራጭ ፕሬዝደንት ባይደን ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር ይህንን ቁጥር ሊቀንሱት ይገባል።”

በወረርሺኙ ጊዜ፣ አምባገነን መሪዎች በጋዜጠኞች ላይ የሚደረገውን የእስራት ትርክት ሊቆጣጠሩት ሞክረዋል፤ ከዚህም በላይ፣ የጋዜጠኞችን የፍርድ ሂደት አጓትተዋል፤ የእስር ቤት ጎብኚዎችን ቁጥር ገድበዋል፤ እስር ቤት ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞችን አስጊ የጤንነት ሁኔታዎች ችላ ብለዋል። በዚህም የተነሳ፣ ቢያንስ ሁለት ጋዜጠኞች በኮቪድ 19 ታመው ህይወታቸው አልፏል። ሲ.ፒ.ጄ፣ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ከ200 በላይ የሚሆኑ የጋዜጠኞች መብት ጥሰቶችን ሰንዷል#ጋዜጠኝነትንነፃ እናውጣ በሚል ዘመቻ አማካኝነትም፣ የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዲፈቱ ለዓለም መሪዎች ጥሪ አቅርቧል።

ሲ.ፒ.ጄ ያካሄደው ቆጠራ የያዘው እስከ ህዳር 22፣ 2013 እኩለ ሌሊት ድረስ ያለውን የእስረኞቸ ዝርዝር ሲሆነ፣ አመቱን ሙሉ ሲታሰሩና ሲፈቱ የነበሩ ጋዜጠኞችን አይጨምርም። እነዚህ ጉዳዮች የተካተቱት http://cpj.org/ ውስጥ ነው። አንድ ጊዜ በሲ.ፒ.ጄ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ጋዜጠኞች፣ ድርጅቱ ከእስር መለቀቃቸውን ወይም በእስር እያሉ ህይወታቸው ማለፉን በማያሻማ መልኩ ካላረጋገጠ በስተቀር በዝርዝሩ ውስጥ እንደተካተቱ ይቆያሉ። ሲ.ፒ.ጄ ባደረገው የመብት ክርክር መሰረት፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ቢያንስ 75 የሚሆኑ እስረኞች ከእስር ጊዜያቸው በፊት እንዲፈቱ ተደርጓል።

***

ሲ.ፒ.ጄ ነጻ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ የጋዜጠኝነትን ነጻነት ለመታደግ የቆመ ድርጅት ነው።

ማስታወሻ ለአርታኢያን፤

የሲ.ፒ.ጄ ዘገባ በአማርኛ፣ በአረብኛ፣ በእንግሊዝኛ ፣ በራሽያኛ፣ በስፓኒሽኛ እና በቱርክኛ ይገኛል። ከሲ.ፒ.ጄ ባለሙያዎች ጋር በተለያዩ ቋንቋዎች ቃለ ምልልስ ማድረግ ይቻላል። ለተጨማሪ መረጃ የሚከተለውን አድራሻ ይጠቀሙ፤[email protected]

የሚዲያ ተጠሪ፣

ቢቢ ሳንታ-ውድ

[email protected]