በዓለም ዙሪያ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቁጥር አዲስ ሪከርድ አስመዝግቧል

ቻይና በዓለም ላይ እጅግ አስከፊ ጋዘጠኞችን አሳሪ በመሆን ቀጥላለች፤ ህንድ እና ሜክሲኮ አስቃቂ አሳሪ ከሚባሉት ሀገሮች ከመጀመሪያዎቹ ተርታ ተሰልፈዋል።

ኒውዮርክ ህዳር 30 2014— በ2013/14 እስር ቤት ውስጥ የታጎሩ የጋዜጠኞች ቁጥር አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል፤ 293 ጋዜጠኞች ለእስር የተዳረጉበት ይህ ዓመት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና በሚዲያ ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች በዓለም ዙሪያ እየተስፋፋ በመጣ ቁጥር፣ ገለልተኛ ዘገባዎችን ያለመታገስ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያንጸባርቃል። በተመሳሳይ፣ 24 ግድያዎች እንደተፈጸሙ የሰነደው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴ የዓመታዊ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቆጠራ እና በፕሬስ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቅኝት እንደሚያሳየው፣ በጋዜጠኞች ላይ ያነጣጠረ ግድያ አሁንም እንደቀጠለ ነው። 

የ2013/14 የሲፒጄ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቆጠራ እንደሰነደው፣ 50 ጋዜጠኞችን እስር ቤት በማጎር፣ በየካቲት 2014 የቤጂንግ የክረምት ኦሊምፒክን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ያለችው ቻይና፣ በአለም ላይ እጅግ አስከፊዋ የጋዜጠኞች አሳሪ ሀገር ሆና ቀጥላለች። ጥር 24፣ 2013 የተደረገውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ በከፍተኛ አፈና 26 ጋዜጠኞችን ያሰረችው ማይናማር ቻይናን ተከትላ  የሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። በመቀጠልም፣ ግብፅ 25፣ ቬትናም 23 እና ቤላሩስ 19 ጋዜጠኞችን በማሰር ይከተላሉ።  የአፕል ዴይሊና የኔክስት ዲጂታል መስራች እና የሲፒጄ 2013/14 ግዌን ኢፊል ፕሬስ ፍሪደም ተሸላሚ (Gwen Ifill Press Freedom Awardee) የሆኑትን ጂሚ ላይን ጨምሮ፣ የሲፒጄ ቆጠራ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ በሆንግ ኮንግ ውስጥ የታሰሩ ጋዜጠኞችንም አካቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ በመጣው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በተጣለው የሚዲያ ገደብ፣ ኢትዮጵያ ከኤርትራ በመቀጠል ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገሮች ሁለተኛዋ እጅግ አስከፊ የጋዜጠኞች አሳሪ ሆና ብቅ ብላለች ።

“ሲፒጄ በአለም ዙሪያ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን በእስር ላይ የሚገኙ  የጋዜጠኞችን ቁጥር በተከታታይ ሲመዘግብ ይህ ስድስተኛ ዓመቱ ነው። እየጨመረ የመጣው ይህ ቁጥር ሁለት የማይነጣጠሉ ተግዳሮቶችን ያንጸባርቃል — መንግስታት መረጃን ለመቆጣጠርና ለማስተዳደር ቆርጠው መነሳታቸውን እና ይህን ጥረታቸውን ደግሞ በድፍረት እየጨመሩበት መምጣታቸውን ነው” ሲሉ የሲፒጄ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ጆኤል ሲሞን ተደምጠዋል። “በዜና ዘገባቸው የተነሳ ጋዜጠኞችን ማሰር የአምባገነን መንግስት መለያ ነው። ከአመት ወደ አመት ብዙ አገሮችን በዚህ ተርታ ሲሰለፉ ማየት በጣም ይረብሻል፤ በተለይ ማይናማርና ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነቱ ላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በራቸውን መጠርቀማቸው በጣም የሚያስደነግጥ ነው።

የመጀመሪያዎቹ አስሩ ዋና አሳሪ ሀገራት ውስጥ ቱርክ፣ ኤርትራ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ሩሲያ እና ኢራን ይገኙባቸዋል። በነዚህ ሀገራት፣ መሪዎች የቴክኖሎጂ እና የደህንነት ህጎችን በመደበኛነት ተቃውሞን ለማፈን እና አለማቀፍ ደንቦችን ያለ ከልካይ ለመጣስ እንደ መሳሪያ ይጠቀሙባቸዋል። በአለም አቀፍ ደረጃ፣ በመንግስታት ላይ የሚቀርቡ ክሶች በጣም እየተለመዱ መጥተዋል፤ ነገር ግን፣ በዚህ አመት ሲፒጄ ቢያንስ 17 የታሰሩ ጋዜጠኞች በሳይበር ወንጀል እንደተከሰሱ ሰንዷል። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ በመስመር ላይ የታተመ ወይም የተሰራጨ ማንኛውም ነገር በወንጀል ሊያስከስስ ይችላል።

አውሮፓ ውስጥ፣ጋዜጠኛ ራማን ፕራታሴቪች በቁጥጥር ስር ለማዋል ስትል የንግድ አውሮፕላንን በሚያሳፍር መልኩ የጠለፈችው ቤላሩስ በአሁኑ ጊዜ 19 ጋዜጠኞችን ለእስር ዳርጋለች። ይህ አሃዝ ሲፒጄ ስለ ታሰሩ ጋዜጠኞች መረጃ መሰብሰብ ከጀመረ ክ1984 ወዲህ በሀገሪቱ የተመዘገበ ከፍተኛው ቁጥር ነው። በላቲን አሜሪካ፣ ከዚህ ቀደም በታሪክ እንደተስተዋለው፣ በእስር ላይ ያሉ ጋዜጠኞች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ቅሉ፣ በኩባ 3፣ በኒካራጓ 2፣ በብራዚል ደግሞ 1 ጋዜጠኞች ታስረዋል፤ በክልሉ ያለው  የፕሬስ ነፃነት ስጋትም ተባብሷል።

የታሰሩ ጋዜጠኞች ቆጠራ ቀነ ገደብ እስከተጠናቀቀበት ድረስ በሰሜን አሜሪካ አንድም ጋዜጠኛ አልታሰረም። ይሁን እንጅ፣ የሲፒጄ አጋር የሆነው የአሜሪካ  የፕሬስ ነፃነት አነፍናፊ (U.S. Press Freedom Tracke) በ2013/14 በመላው አሜሪካ 56 ጋዜጠኞች ለእስር እንደተዳረጉ መዝግቧል፤ ከነዚህ ውስጥ፣ አብዛኛዎቹ የተከሰቱት በተቃውሞ ሰልፎች ወቅት ነው።

እንደ ቱርክ እና ሳዑዲ አረቢያ ያሉ ሀገራት ካለፉት አመታት በተሻለ ጋዜጠኞችን ወደ እስር ቤት ማስገባቱን የመቀነስ አዝማሚያ እያሳዩ ቢመስልም፣ ይህ ሁኔታ የፕሬስ ነፃነት መሻሻል ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባውም። ይልቁንም፣ እንደ ስለላ እና ኢንተርኔት መዝጋትን ያሉ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም እና ነፃነትን በሚገድብ መልኩ እስረኞችን በመፍታት፣ ባለስልጣናት  የሳንሱር ቁጥጥርን  እያስፋፉት ነው።

በአለም አቀፍ ደረጃ፣ ህንድ፣ ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ቁጥር የላቸው ጋዜጠኞችን (ማለትም አራት ጋዜጠኞችን) መግደሏ ተረጋግጧል። አንድ ሌላ ጋዜጠኛ ደግሞ የተቃውሞ ሰልፍ በመዘገብ ላይ እያለ ተገድሏል። ይሁን እንጅ፣ ሶስት ጋዜጠኞች የተገደሉባት እና የሌሎች ስድስት ጋዜጠኞች ግድያ ደግሞ ከስራቸው ጋር ግንኙነት  ያለው መሆን አለምሆኑ እየተጣራ ያለባት ሜክሲኮ፣ በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙት ሀገራት መካክል ለጋዜጠኞች በጣም አደጋኛ ሀገር ሆና ቀጥላለች። 

በዚህ አመት በዓለም ዙሪያ ከሞቱት ጋዜጠኞች መካከል፣ 80 በመቶ የሚሆኑት ህይዎታቸውን ያጡት ግድያ ተፍጽሞባቸው ነው።በዲሞክራሲያዊም ሆነ  በአምባገነን መንግስታት ዘንድ፣ በጥፋት አለመከሰስ እየተለመደ መጥቷል፤ ይህ ደግሞ፣ ወንጀለኞች  በጥፋታቸው አይጠየቁም የሚል መጥፎ መልዕክት እያስተላለፈ ነው።

በዚህ ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስ አዲስ የውጭ ፖሊሲ ማዕከል የሆነው የዲሞክራሲ ጉባኤ ይካሄዳል፤ በዚህ ጉባኤ፣በሲፒጄ የታሳሪ ጋዜጠኞች ቆጠራ የተካተቱ ቢያንስ ሰባት ሀገራት ይሳተፋሉ። ከእነዚህ ሀገራት መካከል፣ ብራዚልን፣ ህንድን፣ ኢራቅን እና ፊሊፒንስን ጨምሮ በርካታዎቹ  በመጥፎ ምግባራቸው ቅጣት ያልተላለፈባቸው ናቸው።  ባለሥልጣናቶቻቸውም  እንደ የዘንድሮዋ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊዋ ማሪያ ሬሳ ባሉ ገለልተኛ ጋዜጠኞች ላይ የበቀል እርምጃ መውሰዱን የቀጠሉ ናቸው፤ በዚህ ሳምንትም፣ በማሪያ ሬሳ ላይ ሌላ የፈጠራ ክስ መስርተውባታል።

በሲፒጄ የቀረበው አሳዛኝ ሪፖርት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሲፒጄ በዜና ዘገባ ላይ የሚደረግ ሳንሱርን መፋለሙን ይቀጥላል። ሲፒጄ ባደረገው ትግል የተነሳ፣ በአለም ዙሪያ ቢያንስ 100 የታሰሩ ጋዜጠኞች ከፍርድ ጊዜያቸው ቀድመው ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል። በቅርቡ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ አለም ለዕውነት (A Safer World For The Truth) ዘመቻ አካል የሆነውን የህዝብ  ችሎት (People’s Tribunal)፣ ሲፒጄ እና አጋሮቹ አስጀምረዋል፤ የችሎቱ አላማም፣ በጋዜጠኞች በሚደርስ ግድያ የተሳተፉ ወንጀለኞችን  ያለመከሰስ ሁኔታ መሞገት ነው። የሰፈው ማህበርሰብ ቅርጽ ያለው ይህ ችሎት፣ ምርመራዎችን እና ከፍተኛ ጥራት ያለውን የሕግ ትንተና መሰረት በማድረግ፣ ለአንዳንድ የተወሰኑ የክስ ጉዳዮችን የፍትህ እና የተጠያቂነት ማዕቀፍ ያዘጋጃል።

የሲፒጄ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቆጠራ፣ እስከህዳር 22፣ 2014 እኩለ ሌሊት ላይ፣ 06፡01  የተጠናቀረ እና የታሳሪዎችን ዝርዝር የያዘነው። በዓመቱ ውስጥ ታስረው የተፈቱትን በርካታ ጋዜጠኞችን አያካትትም። የእነዚያ ጉዳዮች መረጃ በሲፒጄ ድረ-ገጽ (http://cpj.org) ላይ ይገኛሉ። ሲፒጄ በስራቸው የተነሳ የተገደሉ ጋዜጠኞችን  የተነተነበት መረጃ እስከ ህዳር 22፣ 2014 የተሰበሰበን መረጃ መሰረት ያደረገ ነው።  ይህ የሲፒጄ መረጃ (cpj.org/data/killed/) ያለማቋረጥ ይሻሻላል።

***

ሲፒጄ ገለልተኛ እና ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በዓለም ዙሪያ የፕሬስ ነፃነትን ለመጠበቅ የሚሰራ ድርጅት ነው።

ማስታወሻ ለአርታዒዎች፤

የ ሲፒጄ ዘገባ በደረ-ገጹ (cpj.org ) ላይ በብዙ ቋንቋዎች ይገኛል። የሲፒጄ ባለሙያዎች ለቃለ መጠይቅ ዝግጁ ናቸው።