የካሽሚሪ ጋዜጠኞች በህንድ ቁጥጥር ስር በወደቀችው ካሽሚር፣ ስሪናጋር ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት ከተቋረጠ ከ100 ቀናት በኋላ ማለትም ህዳር 2፣ 2012 መፈክሮችን እና ተቃውሞዎችን አሰምተዋል። በአለም ዙሪያ ያሉ ጋዜጠኞች የኢንተርኔት አገልግሎት በሚቋረጥበት ጊዜ ለመስራት ይቸገራሉ፤ የኢንተርኔት መዝጋት ድንጋጌዎች የሚተላለፉት ብዙ ጊዜ በአመጽ ወይም በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ወቅት ነው። (ኤፒ ፎቶ/ሙክታር ክሃን)

ዲጅታል ደህንነት፤ የኢንተርኔት መዘጋት

የኢንተርኔት መዘጋት ለፕሬስ ነፃነት ከባድ መዘዝ እንዳለው እና ጋዜጠኞችንም ስራቸውን በብቃት ለማከናዎን አዳጋች እያደረገባቸው እደሆነ ሲፒጄ አረጋግጧል። ኢንተርኔት ተዘጋ ወይም ተገደበ ማለት፣ የሚዲያ ሰራተኞች አንድ ሁነት እስኪፈጠር ድረስ ምንጮችን ማግኘት፣ የመረጃን እውነታ ፍተሻ ማድረግ ወይም ታሪኮችን መሰነድ አይችሉም ማለት ነው። ኢንተርኔት ሊዘጋ የሚችለው ባብዛኛው በግጭት፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት ወይም በምርጫ ወቅቶች ሲሆን፣ እንደ አክሰስ ናው (Access Now) ያሉ አለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች እንደሚሉት፣ መንግስታት እነዚህን አጋጣሚዎች የሚጠቀሙት የህዝቡን የመረጃ ተደራሽነት ለመገደብ ነው።

የተለያዩ የኢንተርኔት መዘጋት ዓይነቶች ያሉ ሲሆን፣ በመላው ሀገር ወይም በተወሰኑ ክልሎች ብቻ ሊከሰቱ ይችላሉ። ሙሉ በሙሉ የመዘጋት ችግር የሚያጋጥማቸው ጋዜጠኞች፣ የኢንተርኔትም ሆነ የስልክ አግልግሎት ሙሉ በሙሉ ይቋረጥባቸዋል፤ ይህም ማለት፣ ኢንተርኔትን መጠቀም፣ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመስመር ወይም በተንቀሳቃሽ ስልክ መገናኘት አይችሉም ማለት ነው። መንግስታት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎችን፣ የመገናኛ መተግበሪያዎችን ወይም እንደ ዩቲዩብ ያሉ የተወሰኑ ጣቢያዎችን ወይም አገልግሎቶችን እንዲገድቡ ሊያዟቸው ይችላሉ። እንደዚህ አይነቱን አገልግሎት በከፊል የማቋረጥ ሁኔታ የሚዲያ ሰራተኞችን ከሌሎች ሰዎች ጋር የመገናኘት ወይም ይዘትን ኢንተርኔት ላይ የመጫን አቅምን ይገድባል።

የኢንተርኔት ፍጥነትን በመቀነስ ድረገፆች ይዘታቸውን ማሳየት እንዳይችሉና እና ሰዎች ይዘቶችን መጫን እንዲያቅታቸው በማድረግ ኢንተርኔቱን ጥቅመ-ቢስ ማድረግ ሌላው የኢንተርኔት አገልግሎትን የመቆጣጠሪያ ዘዴ ነው።

ከሁሉም አይነት የኢንተርኔት መዘጋቶች ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመቋቋም፣ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። የኢንተርኔት መዘጋት ለሚያሳስባቸው ጋዜጠኞች፣ የሚከተሉት መረጃዎች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።

አጠቃላይ የዲጂታል ደህንነት ምርጥ ተሞክሮ

  • የኢንተርኔት ግንኙነት ከመቋረጡ አስቀድሞ ጥሩ የዲጂታል ደህንነት ተሞክሮዎች ዝግጁነት ካለዎት፣ ኢንተርኔት በሚጠፋበት ጊዜ ዘገባዎችን ለመስራተ በተሻለ ሁኔታ ተዘጋጅተዋል፤ ደህነነተዎንም ለመጠበቅ የተሻላ ዝግጁ ነዎት ማለት ነው።
  • ኢንተርኔት በተዘጋ ጊዜ የዘገባ ስራ እየሰሩ ለእስር ቢዳረጉ፣ እርስዎን እና ምንጮችዎን ከአደጋ ለመጠበቅ መሳሪያዎቸዎን በሚስጠር ይያዙ፤ በእነሱ ላይ የሚያኖሩትን መረጃም ይመስጥሩ።
  • ከሌሎች ጋር ለመገናኘት ከጫፍ እስከ ጫፍ የተመሰጠሩ የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎችን ይጠቀሙ። ከጫፍ እስከ ጫፍ ምስጠራ ማለት ጥሪዎችን ጨምሮ በመተግበሪያው የሚላኩ ይዘቶች የተመሰጠሩ ይሆኑና እና በማስተላለፍ ሂደትም ሊጠለፉ አይችሉም ማለት ነው። ሲግናል ወይም ዋትስአፕ ለዚህ እንደማሳያነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ኩባንያዎች የመልዕክቱን ምንነት ማግኘት የማይችሉ ስለሆነ መንግስትም መረጃን እንዲሰጡ አይጠይቃቸውም።

ስለመሣሪያ ደህንነት እና ስለተመሰጠሩ ግንኙነቶች የበለጠ ለመረዳት የሲፒጄን ዲጂታል የጥንቃቄ ኪት (CPJ Digital Safety Kit) ይመልከቱ። 

የኢንተርኔት መዘጋትን በተመለከት ዝግጅት ማድረግ

  • ኢንተርኔት ወይም ግንኙነቶች መቼ ሊቋረጡ እንደሚችሉ ይተንብዩ። ይህ የሚሆነው፣ ምናልባትም የሕዝባዊ አመፅ ሲኖር፣ በተቃውሞ ሰልፎች እና በምርጫ ወቅቶች ነው። በሀገርዎ ውስጥ ከሚገኙ ክልሎች ውስጥ አንዳንዶቹ ለኢንተርኔት እገዳዎች ይበልጥ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
  • መንግስታት የሚያደርጉትን የኢንተርኔት አገልግሎትን እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን እንዲዘጉ የሚያስችል የህግ ለውጦችን በዓይነ ቁራኛ ይከታተሉ። የኢንተርኔት እና የተግባቦት መዘጋትን በተመለከተ በአካባቢው ያሉ ሌሎች መንግስታት ምን እየሰሩ እንዳሉም ጥናት ያካሂዱ።
  • ሙሉ ለሙሉ የኢንተርኔት መዘጋትን አስመልክቶ ስላለዎ እቅድ ከዜና ክፍልዎ እና ከስራ ባልደረቦቸዎ ጋር ይነጋገሩ። የትና መቼ በአካል መገናኘት እንደምትችሉ እና ኢንተርኔትን ሳይጠቀሙ መረጃን እንዴት እንደሚሰንዱ እና ለአርታዒዎች እንደሚያስተላልፉ የሚገልጽ ዝርዝር እቅድ ያውጡ። የመደበኛ ስልክ አድራሻ ዝርዝሮችን ማጋራትን ያስቡ፤ ነገር ግን፣ የመደበኛ ስልክ ግንኙነቶች ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ስለሆነ፣ ሚስጥራዊ የሆኑ የመረጃ ልውውጦችን ማድረግ እንደሌለብዎ ልብ ይበሉ። የኢንተርኔት መዘጋት ስጋት ባላባቸው ክልሎች ወይም አካባቢዎች የሚኖሩ እና የሚሰሩ የስራ ባልደረቦችዎን መደገፍ የሚያስችል እቅድ ይኑርዎ።
  • ሊያስፈልጉዎት የሚችሉ ሰነዶችን ወይም ይዘቶችን ኢንተርኔት ከመዘጋቱ አስቀድመው ያትሙ።
  • ኢንተርኔት በሚዘጋበት ጊዜ፣ መረጃን ለማከማቻ የሚያገለግሉ የዩኤስቢ ድራይቭ ወይም ሲዲ ለሰራተኞች ያቅርቡ።

ትክክለኛ መሳሪያዎችን ይምረጡ

የመስመር ላይ መሳሪያዎች እና አገልግሎቶች ለደህንነት ጥሰቶች ተጋላጭ ናቸው። በተለይ እንደ የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ያሉ የመገናኛ መሳሪያዎችን በተመለከተ፣ ጋዜጠኞች ከቅርብ ጊዜ ዲጂታል የደህንነት መረጃዎች ጋር እራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ይመከራሉ። የሚከተለው ምክር ከሚያዚያ ወር 2013 ጀምሮ ወቅታዊ እንደሆነ ልብ ይሏል፤

  • ኢንተርኔት በከፊል በሚዘጋበት ጊዜ፣ የታገዱ ጣቢያዎችን ለመድረስ እንዲረዳዎ የቪፒኤን አገልግሎቶችን ያውርዱ እና ያዋቅሩ። የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢዎች፣ ብዙ ጊዜ ቪፒኤኖችን ያግዳሉ፤ ስለሆነም፣ የተለያዩ አማራጮች እንዲኖሩዎት ይመከራል። አንዳንድ መንግስታት ቪፒኤን መጠቀምን ስለከለከሉ፣ በሀገርዎ ስላለው ህግ ግንዛቤ ይኑረዎት። የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በሚዘጋበት ጊዜ፣ ቪፒኤን ምንም አያግዝዎትም።
  • ከሌሎች ጋር ለመገናኘት ከአንድ በላይ አማራጮች ይኑርዎት። የተለያዩ የግንኙነት መተግበሪያዎችን አውርዶ ማዋቀር፣ አንዱ ቢዘጋ በሌሎቹ መጠቀም ያስችልዎታል። በተለያዩ መተግበሪያዎች ላይ ሊኖሩ ስለሚችሉ የደህንነት እንከኖች ግንዛቤ ይኑርዎት። ለምሳሌ፣ አንዳንድ አገልግሎቶችን ዝም ብሎ እንዳለ ከመጠቀም ይልቅ፣ ምስጠራን ማብራት ሊያስፈልግ  ይችላል። ኢንተርኔት በሚዘጋበት ጊዜ፣ እንደ ያጫጭር መልዕክት መላኪያ ባሉ ደህንነታቸው ባልተጠበቁ መተግበሪያዎች ለመገናኘት ሊገደዱ ይችላሉ፤ ስለዚህ፣ ሚስጥራዊ የሆነ መረጃን እንዴት ባለ መንገድ ማጋራት እንዳለበዎ ልብ ይበሉ።
  • ‘ብሉቱዝ’፣ ‘ዋይፋይ ዳይሬክት’ እና ‘ኒር ፊልድ ኮሙኒኬሽን’ን (NFC) በመጠቀም መረጃን እንዴት ማጋራት እንደሚችሉ ይወቁ። እነዚህ ዘዴዎች ኢንተርኔትን ሳይጠቀሙ ስልክዎን ከሌላ ስልክ ጋር በማጣመር መረጃን ለማስተላለፍ ያስችሉዎታል። እነዚህ ነገሮች፣ በስልክዎ ቅንብሮች ክፍል ውስጥ በመደበኛነት ሊገኙ ይችላሉ። ኢንተርኔት ከመዘጋቱ በፊት እነሱን መጠቀም ይለማመዱ፤ ፋይል ማጋራትን በተመለከተም ያለባቸውን ውስንነትም አስቀድመው ይገንዘቡ።
  • እንደ ‘ብርያር’ (Briar) ወይም ‘ብሪጅፋይ’ (Bridgefy) ያሉ የአቻ ለአቻ መላላኪያ መሳሪያዎችን አውርድው ያዋቅሩ። ብርያር፣ በኢንተርኔት፣ በዋይፋይ ዳይሬክት እና በብሉቱዝ የሚሰራ ከጫፍ እስከ ጫፍ የተመሰጠረ የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያ ነው። ብሪጅፋይ ከብርያር ያነሱ የደህንነት ባህሪያት ያሉት ቢሆንም፣ ለረጅም ርቀት ይሰራል።
  • በተዘዋዋሪ (roaming ) የሚሰራ ዓለም አቀፍ ሲም ካርድ ወይም የሳተላይት ስልክ ካለዎት የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ። ሆኖም፣ እነዚህን አገልግሎቶች መጠቀም ሊያስከትል የሚችለውን የደህንነት ስጋት (በተለይም ያሉበትን ቦታ ከማመልክት አንጻር) ጠንቅቀው ማወቅ ይኖርብዎታል። ዓለም አቀፍ ሲም ካርድ ወይም የሳተላይት ስልክን መጠቅም ህገ-ወጥ መሆን አለመሆኑንም ማጣራት ይኖርበዎታል።

ኢንተርኔት በሚዘጋበት ወቅት፤

  • ኢንተርኔት በሚዘጋበት ወቅት፣ የዘገባ ስራ መስራት እንደየ ሁኔታው ለእስር ይበልጥ ተጋላጭ ሊያደርግዎ ይችላል። ስለሆነም፣ መሳሪያዎችዎ እርስዎን ወይም ሌሎችን አደጋ ሊጥሉ የሚችሉ ምንም አይነት ሚስጥራዊ መረጃዎችን እንዳልያዙ ያረጋግጡ።
  • ምንም እንኳን እየሆነ ያለውን ነገር በዛው ቅጽበት መዘገብ አስቸጋሪ ቢሆንብዎም፣ ሁኔታውን መሰነድ ይችሉ ይሆናል። መረጃን ለማከማቸት እና ለስራ ባልደረቦቸዎ እና ለአርታኢዎች ለማስረከብ ዩኤስቢ ወይም ሲዲ ይጠቀሙ። ከተቻለም፣ መረጃዎቹን ያመስጥሩ። እነዚህ መሳሪያዎች ላይ ያሉትን መረጃዎች ሳይመሰጠሩ እርሰዎ በቁጥጥር ስር ቢውሉ፣ መረጃዎቹ ባለሥልጣናት እጅ ሊገቡ እንደሚችሉ አይዘንጉ።
  • ፋይሎችን ብሉቱዝ፣ ዋይፋይ ዳይሬክትን ወይም ኤንኤፍሲን (NFC) በመጠቀም ያጋሩ። እነዚህ የማጋሪያ መንገዶች ብዙውን ጊዜ በመሣሪያ ቅንብሮች ስር ይገኛሉ። መረጃን በነዚህ መንገዶች ማስተላለፍ የደህንነት ስጋት እንዳለውም ልብ ይበሉ። ስለሆነም፣ መረጃዎን አስተላልፈው እንደጨረሱ ማጥፋት ይኖርብዎታል። ይህን ማድረግ፣ መሳሪያዎ በአቅራቢያው ካሉ ካልታወቁ መሳሪያዎች ጋር ግንኙነት እንዳይመሰርቱ ይረዳዎታል።
  • እንደ ብርያር እና ብሪጅፋይ ያሉ የአቻ ለአቻ የግንኙነት መተግበሪያዎችን ይጠቀሙ። እነዚህ መተግበሪያዎች ያሉባቸውን የደህንነት ስጋቶችም ይወቁ።
  • ኢንተርኔት በሚዘጋበት ጊዜ ሚስጥራዊነት ያላቸውን መረጃዎች ለመለዋወጥ እንደ  ያጫጭር መልዕክት መላኪያ እና የስልክ ጥሪዎች ያሉ ደህንነታቸው ያልተጠበቀ የመገናኛ ዘዴዎችን ከመጠቀም ይቆጠቡ። እነዚህን የመገናኛ ዘዴዎች፣ መንግሥታት (ለምሣሌ፣ በቴሌኮሙኒኬሽን አቅራቢዎች አማካኝነት) ሊጠልፏቸው ወይም ሊደርሱባቸው ይችላሉ። 
  • የአንድሮይድ ስልክ ተጠቃሚዎች ኤፍ-ድሮይድን ( F-Droid ) በመጠቀም የኢንተርኔት ግንኙነት ሳያስፈልጋቸው መተግበሪያዎችን ማውረድ ይችላሉ። አንድሮይድ መተግበሪያን ለመጫን ሌላው አማራጭ የኤፒኬ (APK)ፋይልን መጠቀም ነው። እነዚህ የመተግበሪያ ፋይሎች ከመተግበሪያ መደብር ጋር ሳይገናኙ በመሣሪያዎች መካከል ሊጋሩ ይችላሉ፤ ነገር ግን፣ ለመተግበሪያ መደብር ማጣራት ተገዢ አይሆኑም፤ ስለዚህ እነዚህን ፋይሎች ከሚያምኗቸው ሰዎች ብቻ ይቀበሉ።
  • የታገዱ ጣቢያዎችን ስክሪንሾት በማድረግ ኢንተርኔት መዘጋቱን ይሰንዱ። ይህንን መረጃ በሀገርዎ ወይም በአለም አቀፍ ደረጃ ላሉ የዲጂታል መብት ተሟጋች ድርጅቶች በቀጣይ ቀናት ማጋራት ይችላሉ። ይህን ማድረግ አደጋ ላይ ሊጥልዎት እንደሚችልም ልብ ይበሉ።

ኢንተርኔት ከተዘጋ በኋላ፤

  • የኢንተርኔት መዘጋት ምልክት በሚታይበት ጊዜ ምን ይሰራ እንደነበር እና ምን እንደማይሰራ ከዜና ክፍልዎ ወይም ከስራ ባልደረቦችዎ ጋር ይነጋገሩ።
  • መሳሪያዎችዎን ይገምግሙ፤ ምትክ ያስቀምጡ እና ይዘቱን ወደ ውጫዊ ‘ድራይቭ’ ወይም ወደ ‘ክላውድ’ ያስተላልፉ። ከተቻለም፣ የመረጃዎን ደህንነት ከዚህ በበለጠ ለመጠበቅ መረጃዎን ያመስጥሩት።

ሌሎች ሀብቶች፤

  • የ‘መረጃን አሁኑ ያግኙ (Access Now) ‘ኢንተርኔት መዘጋት እና ምርጫዎች መመሪያ መጽሃፍ’ (Internet shutdowns and elections handbook ) እና ሪፖርት እንዲሁም ‘የተሰባበሩ ህልሞች እና የጠፉ እድሎች’(Shattered dreams and lost opportunities) ስለ ኢንተርኔት መዘጋት የበለጠ መረጃ አላቸው።
  • ዊትነስ (Witness) ስልክዎን ከመስመር ውጭ እንዲሰራ እንዴት ማዋቀር እንደሚችሉ (set up your phone) እና ኢንተርኔት በሚዘጋበት ጊዜ ሁነቶችን እንዴት መሰነድ እንደሚችሉ(how to document ) የሚያስረዳ ዝርዝር መመሪያዎች አሉት።
  • የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢንተርኔት መዘጋት ጊዜ ቱልኪት (shutdown toolkit)፣ ኢንተርኔት በሚዘጋበት ጊዜ ሊፈጸሙ የሚችሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዴት መሰነድ እና ማሳወቅ እንደሚቻል የሚያሳይ ዝርዝር መመሪያን ይዟል።